​ቻምፒየንስ ሊግ፡ ኤትዋል ደ ሳህል አራተኛው የግማሽ ፍፃሜ አላፊ ቡድን ሆኗል

የቱኒዚያው ኤትዋል ደ ሳህል የሊቢያውን አል አሃሊ ትሪፖሊ በአጠቃላይ ውጤት 2-0 በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለ አራተኛው ክለብ ሆኗል፡፡

በሶስ ከተማ በተደረገው ጨዋታ ኤትዋል ለተጋጣሚው አሃሊ ትሪፖሊ ፈተና ሆኖ ያመሸ ሲሆን በኳስ ቁጥጥር፣ የግብ ሙከራ የበላይነትን በመውሰድ እና ጫና ፈጥሮ በመጫወት ከሊቢያው መዲና ክለብ በእጅጉ የተሻለ ነበር፡፡ ከሳምንት በፊት ያለግብ ጨዋታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ኤትዋል ደ ሳህል በከፍተኛ ጫና ጨዋታውን ቢጀምርም በ14ኛው ደቂቃ አምር ማሪ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠረው ግብ ባለሜዳዎቹ በተረጋጋ መንፈስ ጨዋታቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏል፡፡

በተደጋጋሚም የአሃሊ ትሪፖሊን የኃላ መስመር መፈተሽ የቻሉት ኤትዋሎች በሁለተኛው 45 ማሪ በአስደናቂ ሁኔታ ድጋሚ በግንባሩ ገጭቶ ባከለው ሁለተኛ ግብ ጨዋታውን አሸንፈው ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰዋል፡፡ ፈረንሳዊው የኤትዋል ደ ሳህል አሰልጣኝ ሁበርት ቬሉድ በ2016 ቲፒ ማዜምቤን የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ባለቤት ያደረጉት ሲሆን ዘንድሮ ኤትዋል ደ ሳህልን ይዘው የቻምፒየንስ ሊጉ አራት ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡

በግማሽ ፍፃሜው ዩኤስኤም አልጀር ከዋይዳድ ካዛብላንካ ሲገናኝ አል አሃሊ ከኤትዋል ደ ሳህል ሌላኛው ጨዋታ ነው፡፡

ውጤቶች

ዩኤስኤም አልጀር 0-0 ክለብ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ (1-1)

ኤስፔራንስ ስፖርቱቭ ደ ቱኒዝ 1-2 አል አሃሊ (3-4)

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 1-0 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (0-1) (3-2 በመለያ ምት)

ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል 2-0 አል አሃሊ ትሪፖሊ (0-0)

ቀጣይ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች

ዩኤስኤም አልጀር (አልጄሪያ) ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)

ኤትዋል ስፖርቲቭ  ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ከ አል አሃሊ (ግብፅ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *