​ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ ማዜምቤ በግብ ሲንበሸበሽ ክለብ አፍሪካም ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፏል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች እሁድ ሲደረጉ ቲፒ ማዜምቤ እና ክለብ አፍሪካ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የተቀላቀሉበትን ውጤት ማሳካት ችለዋል፡፡ ቲፒ ማዜምቤ የሱዳኑ አል ሂላል ኦብዬድ ላይ 5 ግቦችን አስቆጥሮ ሲያሸንፍ ክለብ አፍሪካ የአልጄሪውን ኤምሲ አልጀር 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
ቲፒ ማዜምቤ 5-0 አል ሂላል ኦብዬድ

የምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው ተወካይ ሆኖ ቀርቶ የነበረው አል ሂላል ኦብዬድ ለመጀመሪያ ግዜ በተሳተፈበት የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አስደናቂ ግስጋሴን አድርጎ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለ ሲሆን በሃያሉ የሉቡምባሺ ክለብ ቲፒ ማዜምቤ ህልም የሚመስለው ጉዞውን ተገቷል፡፡

ከሳምንት በፊት በሜዳው 2-1 በማዜምቤ መሸነፉን ተከትሎ የማለፍ ቅድመ ግምቱን በስፋት ያገኘው የአምናው የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ባለድል ቲፒ ማዜምቤ ነው፡፡ ማዜምቤ በሜዳው አል ሂላል ኦብዬድን ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር 5-0 መርታት ችሏል፡፡ የማዜምቤን የድል ግቦች ኪሊትሶ ካሱሱላ፣ አዳማ ትራኦሬ፣ ንጊታ ማላንጎ (2) እና ኢሳማ ፔኮ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ማዜምቤ የአምና ድሉን ዘንድሮም የመድገም አቅም ላይ የሚገኝ ይመስላል፡፡

ክለብ አፍሪካ 2-0 ኤምሲ አልጀር

በሩብ ፍፃሜው የሁለተኛ በነበረው የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ደርቢ ክለብ አፍሪካ በስታደ ኦሎምፒክ ራደስ ኤምሲ አልጀር 2-0 በመርታት የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫን የወሰዱት ባለሜዳዎቹ ሞታዝ ዘምዘሚ የ21ኛ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት መሪ ሲሆኑ በሁለተኛው 45 ኤምኢ አልጀሮች የአቻነት ግብ ፍለጋ የተከላካይ መስመራቸውን አጋልጠው ሲያጠቁ ተስተውሏል፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ቱኒዚያዊው ቀድሞ የኦሎምፒክ ማርሴይ እና ኢቪዮን አጥቂ ሳብር ካሊፋ በመልሶ ማጥቃት ሙክታር ቤልኬተር ከክለብ አፍሪካ የግብ ክልል ያሻረለትን ኳስ የግብ ክልሉን ለቆ ወጥቶ በነበረው የኤምሲ አልጀሩ ግብ ጠባቂ ፋውዚ ካውቺ መረብ ላይ ኳስን አሳርፎ ክለብ አፍሪካን በአጠቃላይ ውጤት ባለድል አድርጓል፡፡ ሳምንቱ ለቱኒዚያ ክለቦች አስከፊ ቢመስልም ክለብ አፍሪካ እና ኤትዋል ደ ሳህል ዛሬ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ በሁለቱም የአፍሪካ ውድድሮች ቱኒዚያ በግማሽ ፍፃሜው እንድትወከል አስችለዋል፡፡

በግማሽ ፍፃሜው ፉስ ራባት ቲፒ ማዜምቤን ሲገጥም ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ከክለብ አፍሪካ ይገናኛሉ፡፡

ውጤቶች

ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን 1-0 ፋት ዩኒየን ስፖርት (0-1) (4-5 በመለያ ምቶች)

ዜስኮ ዩናይትድ 2-2 ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (0-0)

ቲፒ ማዜምቤ 5-0 አል ሂላል ኦብዬድ (2-1)

ክለብ አፍሪካ 2-0 ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (0-1)

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች

ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት (ሞሮኮ)

ክለብ አፍሪካ (ቱኒዚያ) ከ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (ደቡብ አፍሪካ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *