በትላንትናው እለት የሉቲንያ የጥሎ ማለፍ (LFF Cup) ሲጠናቀቅ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ የሚመራው ስታምብራስ ዛልጊሪስ ቪልኒውስን በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊው አማካይ ሶፎንያስ አስረስም ወደ ዩሮፓ ሊግ ማለፉን ያረጋገጠው ቡድን አባል ነው፡፡
በጨዋታው ስታምብራስ 1-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ብቸኛውን የድል ጎል ናስሮ ቦውቻሬብ በ84ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ስታምብራስ በ2018/19 የዩሮፓ ሊግ ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆኑን ከወዲሁ አረጋግጧል፡፡ ክለቡን በጃንዋሪ 2017 የተረቡትና በ2006 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶም የመጀመርያ ድላቸውን ከክለቡ ጋር አጣጥመዋል፡፡
በክለቡ ስብስብ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ሶፎንያስ መኳንንት አስረስ በቀጣዩ አመት በዩሮፓ ሊግ ላይ ሊጫወት የሚችል ተጫዋች ነው፡፡ የቀኝ መስመር አማካዩ ከስታምብራስ የወጣት ቡድን በ2017 ወደ ዋናው ቡድን ያደገ ሲሆን በተለያዩ የፖርቱጋል ክለቦች የሙከራ ጊዜ አሳልፎ ወደ ክለቡ ተመልሷል፡፡
በዘንድሮው የዩሮፓ ሊግ የአልባንያው ኬኤፍ ስከንደብሩ ወደ ምድብ ጨዋታዎች ሲያልፍ ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢንያም በላይ የቡድኑ አባል እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በ2009 የተመሰረተው ስታምብራስ በፖርቹጋላዊያን ባለሀብቶች የሚተዳደር ሲሆን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶም በክለቡ የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸው ታውቋል፡፡