የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ትላንት እና ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተቋጭቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሰም በይፋ ዋንጫውን አንስቷል፡፡

ትላንት በተደረጉ 5 ጨዋታዎች መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን በተክለወልድ ፍቃዱ እና ግቦች 2-0 ሲረታ ቀጥሎ በተደረገው በሌላው የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ደደቢት መብራ ኃይልን 4-0 አሸንፏል፡፡ ለደደቢት መስፍን ኪዳኔ 3 ግቦችን አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ ሲሰራ ጋናዊው ሳሙኤል ጋንሳ ቀሪዋ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ባህር ዳር ላይ ዳሽን ቢራ አርባምንጭን በዮናታን ከበደ ግብ 1-0 አሸንፎ ሲወጣ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ሐረር ሲቲን 2-1 አሸንፏል፡፡ አበበ ቢቂላ ላይ ደግሞ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ መድን ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡

ዛሬ 2 ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1-0 አሸንፎ የውድድር ዘመኑን በድል አጠናቋል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው አዳነ ግርማ ነው፡፡ በሀዋሳ በተደረገው ሌላ ጨዋታ ሀዋሳ ከነማ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 2-0 ተሸንፏል፡፡

ረቡእ እለት በደደቢት እና መከላከያ መካከል ከሚደረገው ተስተካካይ ጨዋታ ውጪ የውድድር ዘመኑ መርሃ ግብር የተጠናቀቀ ሲሆን ዛሬ በተካሄደው የመዝጊያ ስነ-ስርአትም የኮከቦች ምርጫ እና የዋንጫ ስነስርአት ተካሂዷል፡፡

ሲጠበቅ የነበረው የኮከብ ተጫዋችነት ምርጫ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ኡመድ ኡኩሪ አምርቷል፡፡ ለከርሞ በኢትሃድ አሌሳንድሪያ ማልያ የምንመለከተው ኡመድ አምና ጌታነህ እንዳደረገው ሁሉ የኮከብ ተጫዋችነት እና ግብ አግቢነትን ክብር ተጎናፅፎ ፕሪሚየር ሊጉን ተሰናብቷል፡፡

በውድድር ዘመኑ ጥቂት ግብ ያስተናገደው (አመዛኞቹ ግቦች የተቆጠሩት ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ነው) ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንግካራ የኮከብ ግብ ጠባቂነቱን ክብር ሲወስድ የውድድር ዘመኑ 2/3ኛ ጨዋታዎችን ብቻ የመሩት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ሬኔ ፌለር የኮከብ አሰልጣኝነቱን ክብር ወስደዋል፡፡

በአጠቃላይ የ2006 አም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁማዊ የበላይነት ተተናቋል፡፡ የኮከብ ግብ ጠባቂነት ፣ ኮከብ ግብ አግቢነት ፣ ኮከብ ተጫዋችነት ፣ ኮከብ አሰልጣኝነት እና ቻምፒዮንነት ክብርን ጠራርገው ወስደዋል፡፡

ያጋሩ