የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የ2009ዓም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የክለቦች አመታዊ ስብሰባ እና የ2010 ዓም ሴቶች የ1ኛ እና 2ኛ ዲቪዚዮን ድልድል እጣ ማውጣት ሥነ ስርሃት ዛሬ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል አከናውኗል፡፡
በስብሰባው ላይ በሁለቱም የዲቪዚን ውድድሮች የሚሳተፉ የክለብ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ባሳለፍነው አመት ከነበሩት 20 ክለቦች በተጨማሪ ቄርቆስ ክፍለ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል በውድድሮቹ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት በማሳየታቸው እንደተካተቱ ተገልፃል፡፡
የእለቱን መርሃ ግብር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ የመክፈቻ ንግግር ሲከፈት ፕሬዝዳንቱም ለክለብ ተወካዮች እንደ ወንዶቹ ሁሉ ለሴቶችም ትኩረት እንዲሰጡ ያሳሰቡ ሲሆን በሴቶች እግር ኳስ ላይ በደንብ ከተሰራ የተሸለ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ የኮሚቴ አባላት የየራሳቸውን ሪፖርቶች ለታዳሚያኑ ያቀረቡ ሲሆን በሊጉ ላይ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችም ተዳሰው የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበውባቸዋል፡፡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ወርቁ የ2009 ዓም የሴቶችን ፕሪምየር ሊግ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በቅድሚያ ያቀረቡ ሲሆን በውድድሩ ላይ የተሰሩ ስራዎችን በመዘርዘር ለተወካዮቹ ገለፃ አድርገዋል፡፡
በ2009 ዓም የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ በአጠቃላይ 565 ስፖርተኞች እንደተሳተፉ የተገለፀ ሲሆን በርካታ ብቃት እና ችሎታ ያላቸው የሴት ተጨዋቾች ለማየት እንደተቻለ ተነግሯል፡፡
በሪፖርቱ ላይ በሊጉ ላይ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች የተገለፁ ሲሆን በተለይ በተለይ ግን በነበሩ ደካማ ጎኖች ላይ የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀምጠው ለማሻሻል ጥረቶች እንደሚደረጉ ተገልፃል፡፡
በሊጉ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች በውድድሩ ላይ በመሳተፋቸው የሜዳ ገቢ አለማግኘታቸው አሳሳቢ ጉዳይ እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን ይህንን ለማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩ ተነግሯል፡፡
የብሄራዊ የዳኞች ኮሚቴ በተመሳሳይ የአመቱን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን በአመቱ ላይ የታዩ ችግሮችን ለመዘርዘር ሞክረዋል፡፡
*የሴት ዳኞች ቁጥር ማነስ
*በአንዳንድ ክለቦች ላይ በተደጋጋሚ ዳኞችን የመመደብ ጉዳይ
*አልፎ አልፎ የሚታይ የዳኝነት ስህተቶች መኖራቸው
*በጥቂት ጨዋታዎች ላይ የታዩ የዳኝነት ውሳኔዎችን በፀጋ አለመቀበል እና ሌሎችም እንደነበሩ የተገለፀ ሲሆን በተለይ በተለይ ግን የሴት ዳኞቻችንን ቁጥር የማብዛት ጉዳይ እና የተለያ ስልጠናዎች በማዘጋጀት ዳኞቻችንን የማብቃት ጉዳይ ላይ በ2010 ዓም ጠንካራ ስራዎች እንደሚሰሩ ተጠቁሟል፡፡
የዲሲፕሊን ኮሚቴ እና የፀጥታ ሃይል ኮሚቴ በሊጉ ላይ የታዩ ችግሮች ያስረዱ ሲሆን ከወንዶቹ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሻለ ሰላማዊ እንደነበረ እና የተጋነነ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች እንዳልነበሩ ገልፀዋል፡፡