የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ተጠናቀዋል

የደቡብ ክልል ካስቴል ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም ተካሂደው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፉ ክለቦች ተለይተዋል፡፡

ምድብ ሀ

ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ፋሲል ከተማ

3:00 ሰአት ላይ የጀመረው የኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ፋሲል ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ሆነው የታዩ ሲሆን በ34ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ ያሻገራትን ኳስ ክሪዚስቶም ንታንቢ አስቆጥሮ ቡናን ቀዳሚ በማድረግ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ሲታይበት በሁለቱም በኩል ያለተሳኩ የግብ ሙከራዎች ተስተናግደዋል፡፡ በመጨረሻም በ88ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ኤፍሬም ወንድወሰን ለግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ሲያቀብለው ኳሷ በማጠሯ ፊሊፕ ዳውዝ አጋጣሚውን በመጠቀም በድኑን አቻ አድርጎ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ፋሲል ከተማ የምድብ አንድ መሪ በመሆን ወደ ግማሽ ፍፃሜ በማለፍ አርባምንጭ ከተማን ሲያገኝ ኢትዮጵያ ቡና በ1 ነጥብ ከውድድሩ ተሰናባች ሆኗል፡፡

ሀዋሳ ከተማ 2-2 ወላይታ ድቻ

05:00 ላይ የተካሄደው ጨዋታ በተመሳሳይ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ተመጣጣኝ ፉክክርም በጨዋታው ታይቷል፡፡ ጃኮ አራፋት በቀድሞ ክለቡ ላይ ምልረት የለሽ በሆነበት ጨዋታ በ19ኛው እና 23ኛው ደቂቃ አከተትሎ ባስቆጠራቸው ጎሎች ድቻ በ2-0 መሪነት ወደ እረፍት እንዲያመራ አድርጓል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ፍፁም የበላይነት አሳይቶ አቻ የሆነባቸውን ጎሎች ቢያስቆጥርም ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ በቂ አልሆኑለትም፡፡ 79ኛው ደቂቃ ተስፈኛው ፀጋአብ ዮሴፍ  ከሙሉለም ረጋሳ ጋር በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ውስጥ በመግበት የመጀመርያውን ጎል ሲያስቆጥር መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ሴቾ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በሁለተኝነት ወደ ግማሽ ፍፃሜው በማለፍ ሲዳማ ቡናን የሚገጥም ይሆናል፡፡

ምድብ ለ

ወልዲያ 2-1 ድሬዳዋ ከተማ

7:30 ላይ በተደረገው በዚህ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች ትናንት ከሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ የተመዘዙባቸው 3 ቀይ ካርዶች ያለአግባብ ተሰጥተዋል በሚል ባስገቡት ቅሬታ መሰረት ሱራፌል ዳንኤል እና ያሬድ ዘውድነህ ቀይ ካርዱ ተነስቶላቸው በዛሬው ጨዋታ ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ተንቀሳቀሱት ድሬዎች በ11ኛው ደቂቃ በሱራፌል ዳንኤል ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ወልዲያዎች በኤደም ኮድዞ ጎል አጸፈ መልሰው የመጀመርያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከዕረፍት መልስ ወልዲዎች የተሻሉ ሆነው የታዩ ሲሆን በ66ኛው ደቂቃ ታደለ ምህረቴ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል፡፡

አርባምንጭ ከተማ 3-2 ሲዳማ ቡና

በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች ወደ ግማሽ ፍጻሜው የተሸጋገረበትን ድል አሰመዝግቧል፡፡

በ18ኛው ደቂቃ ወንድሜነህ አይናለም ባስቆጠረው ግሩም ግብ ሲዳማ ቡና ቀዳሚ ሆኖ የመጀመርያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ በ58ኛው ደቂቃ አብይ በየነ የሲዳማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ ለማለፍ ማሸነፍ ግዴታ የሆነባቸው አርባምንጮች ቀይረው ባስገቡት ዮናታን ከበደ (ፎቶ) ልዩነት ፈጣሪነት አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡ ዮናታን በ68ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን ጎል በግምባሩ በመግጨት ሲያስቆጥር በ90ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በተመሳሳይ በግምባር በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል፡፡ ጨዋታው ለጠናቀቅ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩ ደግሞ ቡድኑ አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፈበትን ወሳኝ ጎል በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ሲዳማን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ሲያልፍ በቀጣይም ፋሲልን ከተማን የሚገጥም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *