​ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውጪ ሆናለች

በ2018 ፈረንሳይ ለምታስተናግደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ላይ እየተካፈለ የነበረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በኬንያ በአጠቃላይ ውጤት 4-3 ተሸንፎ ከማጣሪያው መሰናበቱን አረጋግጧል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ሀዋሳ ላይ 2-2 ሃገራቱ መለያየታቸውን ተከትሎ የማለፍ ቅድመ ግምቱ ወደ ኬንያ አጋድሎ ነበር፡፡

በማቻኮስ በሚገኘው የኬንያታ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኬንያ ኢትዮጵያን 2-1 መርታት ችላለች፡፡ ኬንያ በ11ኛው ደቂቃ ካራዞን አኩኖ ግብ አስቀድማ መሪ መሆን ችላለች፡፡ አኩኖ ሀዋሳ በተደረገው ጨዋታ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠሯ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአቻነት ግብ ፍለጋ ይበልጥ ተጭኖ መጫወት የቻለ ሲሆን አለምነሽ ገረመው የሞከረችው ኳስ የግቡ ቋሚ ለትሞ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ቡድኖቹ ወደ ለእረፍት መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው አስቀድሞ የኬንያ ግብ ጠባቂ ሊሊያን አዎር በምርቃት ፈለቀ ላይ በሰራችው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት እራሷ ምርቃት ከመረብ አዋህዳ ኢትዮጵያን አቻ አድርጋለች፡፡

ከእረፍት መልስ ኬንያዎች መሪነታቸው ለማስመለስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ግብ ጠባቂዋ ትግስት አበራ በራሷ ግብ ላይ በ52ኛው ደቂቃ ማስቆጠሯን ተከትሎ ኬንያ ዳግም መሪነቱን ማግኘት ችላለች፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ አጥቂዋን ሴናፍ ዋቁማን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት አማራጫቸውን ቢያሰፉም ጨዋታውን ሌላ ግብ ሳይቆጠርበት በኬንያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ኬንያዎች በተደጋጋሚ ግልፅ ግብ የማስቆጠር እድሎችን አግኝተው በትግስት አበራ ጥረት ግብ ከመሆን ድነዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2016 ፓፑዋ ኒው ጊኒ ላስተናገደችው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ የማጣሪያ ዙር ላይ ደርሳ ከጋና ተሸንፋ የወደቀች ሲሆን አሁኑ የማጣሪያ ውድድር በአንደኛው ዙር ጉዟዋ አብቅቷል፡፡ ኢትዮጵያን ማሸነፍ የቻለችው ኬንያ በቀጣይ የማጣሪያ ዙር ከጋና እና አልጄሪያ አሸናፊ ጋር የምትጫወት ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *