​የሴቶች ዝውውር ፡ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ጠንካራ የዝውውር እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል

ዋናውን እና የወጣቶች ቡድኑን አፍርሶ በሴቶች ቡድኑ ለመቀጠል የወሰነው ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ባለፉት ሁለት አመታት በደደቢት የተወሰደበትን የበላይነት በ2010 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለማስመለስ በዝውውር መስኮቱ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ክለቡ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል አምና 24 ጎሎች በማስቆጠር በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ ሎዛ አበራን ተከትላ ያጠናቀቀችው አይናለም አሳምነው ትገኝበታለች፡፡ ሌላዋ የሀዋሳ ከተማ ጠንካራ ተከላካይ ሰብለ ቶጋ እና የመከላከያዋ ታደለች ለክለቡ የፈረሙ ተጫዋቾች ሲሆኑ በ2009 ክለቡን ለቃ ወደ አአ ከተማ አምርታ የነበረችው ቅድስት ቦጋለም ወደ ንግድ ባንክ ተመልሳለች፡፡ በቅርብ ቀናት ተጨማሪ ተጨዋቾች ወደ ክለቡ ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ የሰማን ሲሆን በተለይ የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ ትግስት አበራ ፊርማዋን ታኖራለች ተብሎ ይጠበቃል ።

ንግድ ባንክ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የግብ ጠባቂዋ ንግስት መዐዛ ፣ የተከላካዮቹ አዳነች ጌታቸው ፣ ሀብታምነሽ እሸቱ እና ፅዮን እስጢፋኖስ ፣ የአማካዮቹ ህይወት ደንጊሶ እና ትግስት ያደታ እንዲሁም የአጥቂዎቹን ብዙነሽ ሲሳይ እና ሽታዬ ሲሳይን ውል ለተጨማሪ ሁለት አመት ሲያራዝም ገነት አክሊሉ ፣ ዳግማዊት መኮንን ፣ እፀገነት ብዙነህ እና ብዙሀን እንዳለ ከክለቡ የለቀቁ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሰረት ከሰኞ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *