አዳማ ከነማ ቡድኑን እያጠናከረ ነው

 

በ2015 የካጋሜ ካፕ ላይ የሚሳተፈው አዳማ ከነማ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ነው፡፡ ቡድኑ የ3 ተጫዋቾችን ፊርማ ማግኘቱንም አረጋግጧል፡፡

የወላይታ ድቻው አማካይ ብሩክ ቃልቦሬ በ1.1 ሚልዮን ብር ለ2 አመት የተስማማ ሲሆን ተጫዋቹ ክለቡን እንዲቀላቀል አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወቱ ተነግሯል፡፡

ብሩክ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በቻን አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የነበረ ሲሆን ከኬንያ ጋር በተደረገው የመልስ ጨዋታም ቋሚ ተሰላፊ ነበር፡፡ ቡድኑ ኬንያን በድምር ውጤት 2-0 አሸንፎ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተጫዋቹን እንዳናገሩትና ለክለቡ እንዲፈርም እንዳግባቡት ተወርቷል፡፡ ብሩክን ለማግኘት ባንክ እና መከላከያ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸውም ታውቋል፡፡

የሲዳማ ቡናው የመስመር እና የመሃል ተከላካይ ሞገስ ታደሰ ሌላው የአዳማ ፈራሚ ሆኗል፡፡ በሲዳማ ቡና ከአሸናፊ ጋር የሰራው ሞገስ በድጋሚ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር መገናኘት ችሏል፡፡

የወላይታ ድቻው የመስመር ተከላካይ እሸቱ መና የክለቡ ሌላው ፈራሚ ነው፡፡ እሸቱ ከክለቡ ጋር ለ2 አመታት 1 ሚልዮን ብር ሊከፈለው ተስማምቶ አዳማን ተቀላቅሏል፡፡

በመከላከል እና የጥንቃቄ አጨዋወት የሚታወቁት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አሁን ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች ለሚከተሉት አጨዋወት ተስማሚ ይመስላሉ፡፡

ቡድኑ ከሳምንት በኋላ በካጋሜ ካፕ ለመሳተፍ ወደ ዳሬሰላም ያቀናል፡፡

ያጋሩ