ፌዴሬሽኑ የ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የአፈፃፀም ሪፖርት ይፋ አድርጓል

የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2009 የኢትየጵያ ከፍተኛ ሊግ የክለቦች አመታዊ ስብሰባ እና የ2010 ዓ.ም. ውድድር የእጣ ማውጣት ስነስርዓት ዛሬ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል አከናውኗል።

የኢትየጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ የእለቱን መርሃ ግብር ሲከፍቱ የከፍተኛ ሊጉን ክለቦች ወደ 2010 ዓ.ም. የውድድር ዘመን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግራቸውን ጀምረዋል። አቶ ጁነይዲ ጉባዔው በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ እና መጥፎ ጎኖች ላይ እንዲወያይ ጥሪ አቅርበው፤ በምሳሌነትም በሊጉ ያለውን ተቀራራቢ ፉክክር በጥንካሬ፣ እንዲሁም በውድድር ዓመቱ መገባደጃ ላይ የተፈጠሩ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችን እንደ ደካማ ጎን አንስተዋል። በፌዴሬሽኑ በኩል ህግን በማስከበር በኩል ክፍተት እንዳለ ያልሸሸጉት ፕሬዘዳንቱ በቀጣይ በ2010 የእግር ኳስ ሂደቱ በሰላም፤ ከዘር፣ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ምኞት ተናግረዋል።

ጅማ አባቡና እግርኳስ ክለብ በ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት የሐዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ዙሪያ ውጤትን ያላግባብ ለማግኘት ጥረት ተደርጓል በሚል ያቀረበው ክስ እስካሁን ውሳኔ ሳይሠጥበት መቆየቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክለቦች በፌዴሬሽኑ ስር በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ በክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን መመሪያ እንደተሠጠ እየተነገረ ይገኛል። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሠጡት አቶ ጁነይዲ ባሻ የውሳኔው መዘግየት ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃር የተከሰተ መሆኑን ገልፀው “ውሳኔ መሰጠት ያለበት ጭብጥ ይዞ፣ ህግ ላይ ተንተርሶ ነው፤ ያለው ነገር ተጣርቶ ሁሉም ግልፅ እንዲሆን እንጂ ካስፈለገ እስካሁን የደረስንበትን ሂደት ነገ ይፋ ማድረግ እንችላለን” ሲሉም ተደምጠዋል።

በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2009 ዓ.ም. ውድድር አጠቃላይ የአፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን አራት የተለያዩ ኮሚቴዎች የየራሳቸውን የስራ አፈፃፀም ለግምገማ አቅርበዋል። በ2009 ዓ.ም. የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችም በየሪፖርቶቹ ቀርበው ለታዳሚያኑ ገለፃ ተደርጎባቸዋል።

አጠቃላይ የአፈፃፀም ሪፖርቱን ያቀረቡት የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባል አቶ ስንታየሁ ወ/ማርያም በውድድር ዓመቱ የስፖርት አፍቃሪው (ተመልካቹ) ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር እና ብቃት ያላቸው ተተኪ ተጫዋቾች መታየታቸው እና በሊጉ ከአፋር ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች መወከላቸውን በጥንካሬነት አንስተዋል። በአንፃሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች እጥረት እና በፀጥታ ችግር ምክኒያት የተፈጠረው የፕሮግራም መቆራረጥ፣ እንዲሁም የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት በውድድር ዓመቱ የተስተዋሉ ችግሮች ነበሩ።

የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሪፖርትን ያቀረቡት አቶ መብራህቱ አዲስ በ2009 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ከ7 ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ 136 ዳኞች እና ከ5 ክልሎች የተወከሉ 33 የጨዋታ ታዛቢዎች ተመዝግበው እንደነበር ገልፀው ሁሉም ዳኞች የአካል ብቃት መመዘኛቸውን በብቃት አልፈው የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎችን መምራት እንደቻሉ ተናግረዋል። በአምናው ውድድር ላይ አንድ ዳኛ ያጫወተው ከፍተኛ የጨዋታ ቁጥርን ስንመለከትም በዋና ዳኝነት 14፣ በረዳት ዳኝነት ደግሞ 17 ጨዋታዎች ድረስ የመሩ ዳኞች ነበሩ። በአንዳንድ ሜዳዎች በቂ የፀጥታ ሀይል አለመኖር፣ በተወሰኑ ክለቦች ዳኞች ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ ዛቻዎች፣ የክለብ አመራሮች በዳኞች ኮሚቴ ስራ ላይ ጣልቃ መግባት እና አንዳንድ የክለብ አመራሮች እና አሠልጣኞች ዳኞችን ለማማለል ያደረጉት ጥረት በዳኝነቱ ላይ እክል የፈጠሩ እንደነበሩ ተነግሯል።

በስብሰባው የፀጥታ እና ስነምግባር ኮሚቴ በአቶ ጌታቸው ገ/ማርያም፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በዋና ኢንስፔክተር ወርቁ ዘውዴ፣ እንዲሁም የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴበአቶ ፍሰሀ ገ/ማርያም አማካኝነት ዓመታዊ አፈፃፀማቸውን ለጉባዔው አሰምተዋል። በዲሲፕሊን ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት ላይ በውድድር ዓመቱ 482 የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ተደርገው 1792 ቢጫ እና 70 ቀይ ካርዶች መመዘዛቸው ተገልጿል። በአጠቃላይም ጥፋት የፈፀሙ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች፣ ክለቦች እና የክለብ አመራሮች 659,000 ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኖ ከዚህ ውስጥ 405,500 ብር ለፌዴሬሽኑ ገቢ ተደርጓል።

ውጤትን በፀጋ አለመቀበል፣ ተመልካችን በምልክት ማነሳሳት፣ የተዛባ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት፣ የጨዋታውን ህግ ጠንቅቆ ባለማወቅ የዳኛን ውሳኔ መቃወም እና በሜዳ ውስጥ ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች እና ዳኞች ክብር አለመስጠት ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምንጭ የነበሩ ዋነኛ ጉዳዮች ሆነው ተጠቅሰዋል። 

ከሪፖርቶቹ በኃላ ከ2010 እስከ 2012 ድረስ የሚያገለግል የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ክለቦች የውድድር ደንብ ማሻሻያ በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ የውድድር ስነስርዓት እና ስፖርት ማዘውተሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ በኩል ቀርቧል።

በስብሰባው ላይ የተቀጡ ክለቦች እና ተጫዋቾች በይቅርታ ስለሚታለፉበት ሂደት፣ ስለ ተጨዋቾች የዝውውር ገንዘብ አከፋፈል መንገድ፣ ባልተከለሉ ሜዳዎች ስለሚፈጠረው የፀጥታ እና ደህንነት ስጋት፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት እና የዳኝነት ችግሮች ከክለቦች ጥያቄዎች ቀርበው የመፍትሄ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ለቀጣይ መደረግ አለባቸው ብለው የሚታሰቡ ጉዳዮች ላይም ውይይቶች ተደርገዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *