ኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ከውጭ ሊያስመጣ ነው

 

ኢትዮጵያ ቡና የግብ ጠባቂ ችግሩን ለመቅረፍ ከውጭ ግብ ጠባቂ ለማምጣት እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ቡና በዲስፕሊን ግድፈት ምክንያት ሙሴ ገብረኪዳንን ማገዱ የሚታወስ ሲሆን ተጫዋቹ ክለቡን የመሰናበት እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ በቡድኑ ውስጥ ልምድ ያለው ግብ ጠባቂ የ1 አመት ቀሪ ኮንትራት የሚቀረው ጌቱ ተስፋዬ ብቻ ነው፡፡ የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር እና አዲሱ አሰልጣኝ ከኤጀንቶች ጋር እየተነጋገሩ ሲሆን ግብ ጠባቂው ከየትኛው ሃገር እንደሆነ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡

በተጫዋቾች ግዢ ላይ የተቀዛቀዘው ኢትዮጵያ ቡና እስካሁን የተረጋገጠ ዝውውርም ሆነ የኮንትራት ማራዘምያ ስምምነት አላደረገም፡፡ ስሙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እየተያያዘ የሚገኘው አስቻለው ግርማ እና የአምናው የክለቡ ከፍተኛ ግብ አግቢ ቢንያም አሰፋ ከክለቡ ጋር ለተጨማሪ አመታት ለመቆየት በድርድር ላይ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

ቡና እስካሁን ከኤፍሬም ዘካርያስ ጋር ሲለያይ ክለቡ ያገዳቸው 3 ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር የመቀጠል እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑም ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ተከላካዩ ሳሙኤል ወንድሙ እና ወጣቱ አማካይ መሃመድ ጀማል ከክለቡ ጋር ያላቸው ኮንትራት የተጠናቀቀ ሲሆን እስካሁን የኮንትራት ማደስ ጥያቄ አልቀረበላቸውም፡፡ ወደ ሃዋሳ ከነማ ማምራቱ የተነገረው ጌቱ ተስፋዬ ደግሞ ከክለቡ ጋር ቀሪ የአንድ አመት ውል ስላለው እንደማይለቅ ታውቋል፡፡

ያጋሩ