​” የቻን ውድድርን ለማስተናገድ ጥያቄ አላቀረብንም ” ጁነይዲ ባሻ

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የ2018ቱን የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ለማስተናገድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ጥያቄ ማቅረባቸውን የኮንፌድሬሽኑ ኦፊሴላዊ ድህረ-ገፅ ቢያስታውቅም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁነይዲ ባሻ የማዘጋጀት ጥያቄ አለመቅረቡን ለሶከር ኢትዮጵያ የሬድዮ ፕሮግራም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውድድሩን የማስተናገድ ፍላጎት አላት ቢባልም ፕሬዝደንት ጁነይዲ ፌድሬሽኑ ለካፍ ጥያቄ አለመቅረቡ አስረድተዋል፡፡ “እኛ አስቀድመን ለ2018 ነበር ለማስተናገድ የጠየቅነው፡፡ ነገር ግን ካፍ ለኬንያ እድሉን ሰጥቶ ነበር፡፡ አሁን ላይ ካፍ ያወጣው መረጃ በየት የተገኘ እንደሆነ አናውቅም፡፡ እኛ ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄውን ለካፍ አላቀረብንም፡፡ አንዳንድ የምስራቅ አፍሪካ በተለይ የኬንያ ስፖርት ጋዜጠኞች ኬንያ ውድድሩን የማታስተናግድ ከሆነ እድሉ ለኢትዮጵያ ይሰጠ የሚሉ ሃሳቦችን ሲያንሸራርሽሩ ነበር፡፡ ግን እኛ ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ አላቀረብንም፡፡” ብለዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ አክለውም ካፍ ኢትዮጵያን ለማዘጋጀት ፍላጎት ያላቸው ሃገራት ስር የመደበበትን ሁኔታ እያጤኑት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የመረጃ ክፍተት ተፈጥሮም ከሆነ ለማጣራት ጥረት እንደሚደረግ ፕሬዝደንቱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በወልዲያ ከተማ ከተሰራው የመሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም በተስቀር የቻን ውድድር ለማስተናገድ የሚያችሉ ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው የጨረሱ ስታዲየሞች የሏትም፡፡ በእንደዚህ ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ በአስተናጋጅነት ስር ውስጥ መካተቷም አስራሚ ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *