ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒየንሺፕ (ቻን) በጥር ወር ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባለች መባሉን ፌዴሬሽኑ ቢያስተባብልም የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን ግን ጥያቄው እንደደረሰው የካፍ የሚዲያ ኦፊሰር ጁኒየር ቢንያም በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁነይዲ ባሻ ለሶከር ኢትዮጵያ ራዲዮ ኢትዮጵያ የቻን 2018 ውድድርን ለማስተናገድ ለካፍ ጥያቄ አለማቅረባቸውን መግለፃቸው ይታወሳል። ቢሆንም የካፍ ሚዲያ ኦፊሰር ጁኒየር ቢኒያም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ከፌድሬሽኑ የአዘጋጅነት ጥያቄ መቅረቡን አስታውቋል። “ኦፊሳላዊ የሆነ ጥያቄ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ደርሶናል። ደብዳቤው የደረሰን አርብ መስከረም 19 ነበር።” ሲሉ ለምን ካፍ ኢትዮጵያን የአዘጋጅነት ጥያቄ ካቀረቡ ሃገራት ተርታ እንዳስቀመጠ አስረድተዋል።
ፕሬዝደንት ጁነይዲ የአዘጋጅነት ጥያቄ መቅረቡን ቢያስተባብሉም ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ከአንድ የፌድሬሽኑ አመራር የተፈረመ የአዘጋጅነት ጥያቄ ለካፍ አርብ ደርሷል። ሆኖም ልክ እንደሞሮኮ እና ኤኳቶሪያል ጊኒ ከመንግስት የተገኘውን ድጋፍ የሚገልፅ ደብዳቤ ከኢትዮጵያ በኩል አለመላኩን ለማወቅ ችለናል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን የአዘጋጅነት ጥያቄ ሙሉ እንዳይሆን ያደርገዋል።
በፌድሬሽኑ ውስጥ ባለው የአሰራር እና የአስተዳደር ክፍተት ምክንያት መሰል ጉዳዮች ሲከስቱ ማየት እና መስማት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ የተለመደ ነው።