​የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዝግጅት፡ ሽረ እንዳስላሴ 

ሽረ እንደስላሴ ከፍተኛ ሊጉን የተቀላቀለው ባሰለፍነው 2009 የውድድር አመት ላይ ነበር። በመጣበት አመትም ለብዙ ቡድኖች ፈታኝ በመሆን በአስገራሚ ጥንካሬ ከምድቡ ሦስተኛ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወቃል። በዘንድሮም አመት የአምናውን ጥንካሬ በመድገም ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

ሽረ እንደስላሴ በ2009 የውድድር ዘመን ክለቡ እንደ ድክመት ወስዶ ያገኘው አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች በብሔራዊ ሊግ በነበረው ተሳትፎ የተጠቀመባቸውን ተጨዋቾች ላይ ተጨማሪ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን ሳይቀላቅል ወደ ከፍተኛ ሊግ ውድድር መግባቱ ፣ አስቀድሞ ወደ ውድድር ቀጥታ ከመግባቱ በፊት በቂ ሁኔታ ቅድመ ዝግጅቱን አለማድረጉ እንዲሁም ለቡድኑ የሚያስፈልጉ ትጥቆች እና ቁሳቁሶች አለመሟላታቸው እንደ ድክመት እንደተወሰደ እና የዚህ ሁሉ ችግር መነሻው ክለቡ አቅም ውስንነት የበጀት እጥረት እንደሆነ ሲገለፅ ለዘንድሮ የውድድር አመት ግን ለክለቡ አስፈላጊ የሆነ በጀት እንደተመደበ፣ ወደ ቡድኑም ቢመጡ ይጠቅማሉ ተብለው የታሰቡትን ተጨዋቾች እንዳመጡ ፣ ዝግጅትም አስቀድመው እንደጀመሩ እና ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመግባት ትልቅ እቅድ እንዳላቸው እየገለፁ ይገኛሉ።

የሽረ አዲስ ፈራሚዎች

ሽረ እንዳስላሴ ከአምናው ስብስቡ 10 በላይ ተጨዋቾችን ሲያቆይ 9 ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡ እነሱም ግብ ጠባቂው ሙሴ ዬሀንስ  (መቐለ ከተማ)፣ ኬናረዲ እንድሪስ (ቡራዩ ከተማ)  ፣ ሸዊት ዮሐንስ ( አአ ፖሊስ )፣ ኄኖክ ብርሃኑ (ኢት/ውሃ ስፖርት)፣ ዘላለም (ነቀምት ከተማ) ሲጋን ሮድሪክ (ካሜሩን/ቦሌ ገርጂ)፣ አሸናፊ እንዳለ (አውስኮድ)፣ ጅላሎ ሻፊ (አውስኮድ) ልደቱ ለማ (ለገጣፎ) ናቸው። ሁለት ተጨዋቾች በሙከራ ጊዜ ላይ የሚገኙ ሲሆን በእንቅስቃሴያቸው የአሰልጣኝ ቡድኑን ማሳመን የሚችሉ ከሆነ ሊፈርሙ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ከነሀሴ መጨረሻ ጀምሮ ዝግጅታቸውን በዛው ሽረ ከተማ እየሰሩ ሲገኙ ባሳለፍነው ሳምንት የመስቀል በአልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ውድድር ላይ በመሳተፍ ከመቐለ ከተማ እና ከመከላከያ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።

አሰልጣኝ ዳንኤል ጸሀዬ ከቡድኑ ጋር አብረው የሚቆዩ ሲሆን አምና ያሳየውን ጠንካራ ተፎካካሪነት ዘንድሮም በመድገም ወደ ፕሪምየር ሊግ ቡድኑን ያስገባል የሚል እምነት በደጋፊዎች እና የክለቡ አመራሮች ላይ እንዳለ ተገልጿል፡፡

ሽረ በ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመርያውን ጨዋታ በሜዳው ውጪ ከኢትዮዽያ መድን ጋር የሚያደርግ ይሆናል።


በከፍተኛ ሊጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል በክረምቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ እና ያለፈው አመት ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ዘንድሮ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ክለቦችን ዝግጅት በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *