ከኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተያይዞ ከቅርብ ወራት ወዲህ የሚወጡት መረጃዎች ሁሉ ከአንድ ሀገርን ከሚወክል ብሔራዊ ቡድን ሊሰሙ የማይገቡ አስደሳች ያልሆኑ ሆነዋል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አዲሱ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶም በተለያዮ ምክንያቶች ብሔራዊ ቡድኑ በተረጋጋ ሁኔታ መዝለቅ አልቻለም።
የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአመታት ሲታማበት የቆየው ለብሔራዊ ቡድኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የካፍ ሆነ የፊፋ ካላደርን መሰረት ያደረገ ጨዋታ አያዘጋጅም ለሚለው ጥያቄ መልስ በሚሰጥ መልኩ ከዩጋንዳ ፣ ዛምቢያ እና ቦትስዋና ጋር ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወት የተደረገ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ወደ ሞሮኮ በማቅናት ከሞሮኮ የሀገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ስብስብ (ቻን) ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል ብሎ እየተጠበቀ ይገኛል።
17 ተጨዋቾችን በመያዝ ወደ ቦትስዋና አቅንቶ በሽንፈት የተመለሰው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮጋር ላለበት የወዳጅነት ጨዋታ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡ ሆኖም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከነበራቸው 17 ተጨዋቾች ብሩክ ቀልቦሬ እና ፍሬው ሰለሞን መጠነኛ ጉዳት ላይ ሲገኙ ጋዲሳ መብራቴ ከቦትስዋና መልስ ሌሎቹ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑ አውቶብስ ሲጓዙ እሱ በግሉ ተጉዟል በሚል ምክንያት ተቀንሷል፡፡ አብዱልከሪም መሀመድ ደግሞ ቤተሰብ ጉዳይ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሌሉ ተጨዋቾች ናቸው። ከቡድኑ ጋር በሌሉት ተጫዋቾች ምትክ ባዬ ገዛህኝ እና ሽመክት ጉግሳ ከቡድኑ ጋር አዲስ የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ሲሆኑ አሰልጣኙ ጥሪ አድርገውላቸው ያልመጡ ተጨዋቾችም እንዳሉ እየተነገረም ይገኛል ።
በነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የብሔራዊ ቡድን አባላት ‹‹የምንገጥመው ጠንካራዋን ሞሮኮ ነው፡፡ ያለ በቂ ዝግጅት ባልተሟላ ቡድን መጫወት ከባድ ነው፡፡›› በሚል ወደ ሞሮኮ ባንሄድ ይሻላል የሚል አቋም የወሰዱ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ‹‹ቡድኑን አሟልቶ ለጨዋታ ማዘጋጀት የአሰልጣኙ ስራ በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ ሞሮኮ ሄዶ መጫወት አለበት፡፡ ለአመታት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አታዘጋጁም ተብለን ስንተች ነበር፡፡ ስናዘጋጅ ደግሞ መሸሽ ተገቢ አይደለም›› የሚል አቋም ይዟል፡፡
ዛሬ ረፋድ ላይ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነዱን ባሻ እና የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ የጎደሉት ነገሮች በዚህ ሁለት ቀን ተሟልተው ወደ ሞሮኮ እንዲሄዱ ከውሳኔ የደረሱ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም በጎደለባቸው ተጨዋች ምትክ ሌሎች ተጨዋቾችን በመጥራት እስከ ቅዳሜ ተዘጋጅተው ቅዳሜ ረፍድ ላይ ወደ ሞሮኮ እንደሚያቀኑ ሰምተናል፡፡ ጨዋታውም ማክሰኞ የሚከናወን ይሆናል ።