በአልባኒያ ዋንጫ የአንደኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን በሜዳው ኮርሲ ከተማ ኬኤፍ አድሪያቲኩ ማሙራሲ ያስተናገደው ስከንደርቡ 9-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል፡፡ ኢትዮጵያው ቢኒያም በላይ ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጫወት ችሏል፡፡
ቢኒያም ወደ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ለመካተት አንድ ወር አስፈልጎታል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ስኬንደርቡ በአልባኒያ ዋንጫ ማሙራሲን ከሜዳው ውጪ 8-0 ሲረታ ቢኒያም ተሰልፎ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ ከዛ ጨዋታ በኃላ ክለቡ ባደረጋቸው የሊግ እና የዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች አንዳንዴ በተጠባባቂነት እንዲሁም ከቡድኑ ስብስብ ውጪ እየሆነ ቆይቷል፡፡
የስኬንደርቡ ፍፁም የበላይነት በታየበት ጨዋታ የድል ግቦቹን ኔስፖር (2)፣ ሽኮርዳ፣ ማራ (3)፣ ሊኬሪ፣ ሉላ እና ታኮ ሲያስቆጥሩ ለአንደኛ ዲቪዚዮን ክለቡ ማሙራሲ የማስተዛዘኛ ግብ ያስገኘው ቱንግሺ ነው፡፡ በጨዋታው ላይ ስኬንደርቡ አብዛኞቹን ቋሚ ተሰላፊዎቹን ያሳረፈ ሲሆን በአጠቃላይ ውጤት 17-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡
ስኬንደርቡ ምንም እንኳን በዩሮፓ ሊግ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ቢያገኝም የአልባኒያን ሱፐር ሊጋ በ10 ነጥብ መምራት ጀምሯል፡፡ ክለቡ አምና የተቀማውን የሊግ ክብር የማስመለስ እድሉ የሰፋ ይመስላል፡፡