-የ2 አመት እገዳ እና የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል
-በኃይለየሱስ እና ዘካርያስ ምትክ ሁለት አዲስ ኢተርናሽናል ዳኞች ተመርጠዋል
-‹‹ፍትሃዊ ውሳኔ ካላገኘሁ ከስራዬ ራሴን አገላለሁ፡፡ ወደፊትም ለማቆም የተገደድኩባቸውን ምክንያቶች ይፋ አደርጋለሁ››
ያለፉትን አራት አመታት በኢንተርነሽናል ዳኝነት ያገለገለው እና በቅርብ አመታት ከታዩ ምስጉን አርቢትሮች አንዱ የሆነው ኃይለየሱስ ባዘዘው በ2009 የውድድር አመት እሱ በማያውቃቸው የተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ጨዋታዎችን እንዳያጫውት እንደተደረገ ፣ ከሚመደብባቸው ጨዋታዎችም ቢሆን የተለያየ ምክንያት እንዲቀየር መደረጉን ይገልፃል፡፡ በተለይ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባቡና ከወላይታ ድቻ ጅማ ላይ፣ ድሬደዋ ከተማ ጅማ አባቡና ድሬደዋ ላይ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት እንደሚመራ ተነግሮት ወደ ቦታው እያመራ በማያውቀው ምክንያት መቀየሩ እየተነገረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው የኢንተርናሽናል ዳኞች ዝርዝር እንደሚያሳየው ፌዴሬሽኑ 7 ኢንተርናሽናል ዳኞችን መርጦ ለፊፋ ልኳል፡፡ በዝርዝሩ ላይም ከዚህ ቀደም ኢንተርናሽናል ዳኞች የነበሩ 5 ዳኞች (ባምላክ ተሰማ ፣ በላይ ታደሰ ፣ አማኑኤል ኃይለስላሴ፣ ለሚ ንጉሴ፣ ብሩክ ያነብርሃን) ከዚህ ቀደም ኢንተርናሽናል የነበሩ ሲሆን በፌዴራል ዳኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት ዳዊት አሳምነው እና ቴዎድሮስ ምትኩ ስማቸው ለፊፋ ከተላኩት መካከል ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ኢንተርናሽናል ዳኞች የነበሩት ኃይለየሱስ ባዘዘው እና ዘካርያስ ግርማ ደግሞ አዲስ በታጩት ተተክተው ፈተናውን ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን የሰጠው ኃይለየሱስ ባዘዘው የዳኝት ፈተናውን አልፎ ሳለ አላግባብ ከዝርዝሩ እንደወጣ ገልጧል፡፡
‹‹ በ2010 ኢትዮዽያን በኢንተርናሽናል ዳኝነት በካፍም ሆነ በፊፋ እንዲሁም በኢትዮዽያ ሊጎች ለሚያጫውቱ ዳኞች ባሳለፍነው አመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ያሉበትን የአቅም ደረጃ ለመለካት የተሰጠውን የአካል ብቃት ፈተና በሚገባ ተፈትኜ አልፌያለሁ፤ ፈተናውን የሰጠው የካፍ ኢንስተራክተርም ፈተናውን በማለፌ እንኳን ደስ አለህ የሚል መልክት ልኮልኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ፈተናውን እዳላለፍኩ የተነገረኝ፡፡ መውደቁን ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ወድቀሀል ብባል እንኳ ሌሎቹ ፈተናውን ወድቀው ሁለተኛ እድል እንዳገኙት ዳኞች ሁሉ ለእኔም ሁለተኛ የሙከራ እድል ሊሰጠኝ ይገባል በማለት ማመመልከቻ ባስገባም እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ›› ብሏል፡፡
የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአመቱ ምስጉን ዳኛ ተብሎ የተመረጠው ኃይለየሱስ አሁን ያለበትን ሁኔታ እና የወደፊቱን እንዲህ ተናግሯል፡፡
‹‹ ግልፅ በሆነ መንገድ የደረሰብኝ በደል ነው፡፡ እኔም እንደ ሌሎቹ ዳኞች በእኩል አይን ታይቼ ሁለተኛ የሙከራ እድል እንዲሰጠኝ ጠይቄ ምላሽ እየጠበቅኩ ነው፡፡ ነገ ወይም ከነገ በስቲያ አአ በመምጣት ከተለያዩ አመራሮች ጋር ውይይት አደርጋለው፡፡ ምላሹም መልካም ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ግልፅ እና ፍታኸዊ አሰራር ከመጣ በዳኝነቱ እቀጥላለው፡፡ ያ የማይሆን ከሆነ ግን ለስፖርቱ የሚበጁ እና የሚጠቅሙ ግልፅ የሆኑ አመራሮች እስኪመጡ ድረስ ራሴን ከዳኝነቱ ላገል እችላለው፡፡ ወደ ፊት በዳኝነቱ የማልቀጥል ከሆነ በዝርዝር ለማቆም የተገደድኩባቸውን ምክንያቶች ይፋ አደርጋለሁ፡፡ ››
ከፌዴሬሽኑ አካባቢ እየወጡ እንዳሉት መረጃ ከሆነ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ለሚዲያ ሀሳቡን በመግለፁ ምክንያት የ2 አመት እገዳ እና 40ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈበት ለማወቅ ተችሏል፡፡