በቅርብ አመታት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከተመለከትናቸው ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ መካከል ጋቶች ፓኖም በኢትዮጵያ ቡና ካሳለፈው የስድስት አመት ቆይታ በኃላ ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ሩሲያ በማምራት በክረምቱ የዝውውር መስኮት አንዚ ማካቻካላን መቀላቀሉ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ጋቶች በአንዚ ቆይታው በሩሲያ ዋንጫ ጨዋታ ክለቡ ሽንፈት ሲገጥመው ለመጀመሪያ ግዜ የተሰለፈ ሲሆን በሊግ ውድድር አስካሁን ጨዋታዎችን ማድረግ አልቻለም፡፡ ጋቶች ወደ ሩሲያ ካመራ በኋላ የመጀመርያ የሆነውን ቃለምልልስ ከሶከር ኢትዮጵያው ኦምና ታደለ ጋር አድርጓል፡፡
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ለቀህ ወደ አንዚ ማካቻካላ ያደረከው ዝውውር አነጋጋሪ ነበር፡፡ ወደ አውሮፓ ያደረግከውን ሽግግር እንዴት ትመለከተዋለህ?
“ሽግግሩ በጣም እንደሚታወቀው እጅግ በጣም የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም በአውሮፓ የሚከተሉት የስልጠና ዘዴ እና አጨዋወታቸው የተለየ መሆኑ ሽግግሩም በዛው ልክ እንዲለይ አድርጎታል እላለው፡፡ አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከሃገር ወጥቶ የመጫወት ህልሜ ነው የተሳካው፡፡ ለዚህ ዝውውር መሳካት የረዱኝን ቤተሰቦቼን፣ ወኪሎቼ ዴቪድ በሻ እና ራሶ ቡላቶቪችን ማመስገን እፈልጋለው፡፡”
በሩሲያ እያሳለፍክ ያለው ህይወት ምን ይመስላል ወደ አዲስ ባህል እንደመቀላቀልህ በእግርኳስ ህይወትህ ላይ የፈጠረብህ ተፅዕኖስ ምን ይመስላል?
“በሩሲያ እየመራሁት ያለው የእግርኳስ ህይወቴ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ እስካሁን ይህ ነው ብዬ የምገልፅልህ መጥፎ ጉዳይ ወይም ፈተና አላጋጠመኝም፡፡ ፈተና የሆነብኝ ነገር ቢኖር ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የቡድን አጋሮቼም ሆኑ አሰልጣኞቻችን የእንግሊዝኛ ቋንቋን አይናገሩም፡፡ ይህ ደግም ወደ ሩሲያ ስመጣ ያስቸገረኝ ነገር ነው፡፡”
ለአንዚ ዋናው ቡድን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ለመካተት ወራቶችን መጠበቅ አስፈልጎሃል፡፡ በእርግጥ ከኢትዮጵያ እንደመዛወርህ ሊጉን በፍጥነት ትላመደዋለህ የሚል ግምት የለም…
“አዎ እንዳልከው ለአንዚ ዋና ቡድን ለመጫወት ግዜ ፈጅቶብኛል፡፡ ምክንያቱም እኔ ለሊጉ አዲስ ነኝ፡፡ ክለቤ ወደ ስሎቬኒያ ለቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ሲያመራ በቪዛ ችግሮች ምክንያት አብሬ መጓዝ አልቻልኩም፡፡ ስለዚህም የነበረኝ አማራጭ ከወጣት ቡድኑ ጋር በሩሲያ ቆይቶ ዝግጅት ማድረግ ነበር፡፡ ከወጣት ቡድኑ ጋር ያደረኩት ቆይታ የሩሲያ የእግርኳስ ባህልን እንድላመድ አስችሎኛል፡፡ በወጣት ቡድኑ እና በዋናው ቡድኑ መካከል የሰፋ ልዩነት አለመኖሩ እኔን ጠቅሞኛል፡፡ ለዋናው ቡድን በተሰለፍኩበት የመጀመሪያ ጨዋታዬም የተለየ አይደለም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መጫወት በመቻሌ በመጀመሪያ ጨዋታዬ ላይ የፈጠረብኝ የተለየ ችግር የለም፡፡ የሚጫወቱትን የአጨዋወት አይነት እየተላመድኩ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ነገሮች አሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡”
አንዚ በሊግ ውድድር በመጥፎ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ባስመዘገባችሁት ደካማ ውጤት ምክንያት በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ትገኛላችሁ እንዲሁም ከጥሎ ማለፍ ውድድሩ በግዜ ተሰናብታችኋል…
“አንዳልከው ቡድናችን በጥሩ ሁኔታ ላይ አይገኝም፡፡ ብዙ ጨዋታዎችን መሸነፋችንን ተከትሎ በወራጅ ቀጣው ውስጥ ተገኝተናል፡፡ የቡድናችን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴም መልካም አይደለም፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎች መሻሻሎችን አሳይተን ከወራጅ ቀጠናው እንደምንወጣ ተስፋ አለኝ፡፡ ለእኔ ግን ይህ ለመማር መልካም አጋጣሚ ነው የሆነልኝ፡፡ ቡድናችን የሚከተለውን አጨዋወት እያየሁ ከፊቴ ስለሚጠብቀኝ ፈተና እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዴት አድርጌ ማለፍ እንደምችል ነው ያስተማረኝ፡፡”
ወደ ሩሲያ ስትዛወር በኢትዮጵያ እግርኳስ አፍቃሪያን አዕምሮ ውስጥ ከሚመጡ ነገሮች አንዱ በምስራቅ አውሮፓ እግርኳስ ስለተንሰራፋው እና በአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ላይ ስለሚሰነዘሩ የዘረኝነት ጥቃቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
“በሩሲያ ዘረኝነት አለ፡፡ ቢሆንም ግን አሁን ላይ በአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ላይ የሚደርሰው የዘረኝነት ጥቃት በእጅጉ ቀንሷል፡፡ አሁን ላይ በሊጉ በርካታ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች አለን፡፡ እኔ እስከማውቀው አሁን ላይ የደረሰ ነገር የለም፡፡ ምንአልባት እኔ እንደማስበው የአስተሳሰብ ለውጥ እየመጣ መሆኑ ዘረኝነት በእግርኳስ ሜዳ የቀነሰው ይመስለኛል፡፡”
ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ልክ እንደአንተ ከሃገር ወጥቶ የመጫወቱን ባህል አሁን ላይ እያዳበሩ ይገኛሉ፡፡ እንደሚጠበቀው ባይሆንም ተጫዋቾቻችን ከሃገር ወጥተው የመጫወት እድልን እያገኙ ነው…
“በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አለኝ፡፡ እድል አለማግኘታችን ነው ወደ ውጪ ወጥተን እንዳንጫወት ያደረገን፡፡ እድሉን የሚያመቻችልን ድልድይ አለመኖሩ ነው እንጂ በርካታ አቅሙ ያላቸው ተጫዋቾች በኢትዮጵያ አሉ፡፡ ነገር ግን በአካል ብቃት ላይ ከፍተኛ ልምምድ እና ስራ መስራት አለብን፡፡ ይህ ነው ከሌሎቹ ጋር ልዩነታችን፡፡ በቴክኒኩ ረገድ በጣም የሰፋ ልዩነት የለንም፤ ቢሆንም ግን ከሁሉም በላይ አካል ብቃት ላይ ስራ መስራት አለብን፡፡ በተጨማሪም ወኪሎች ወይም እግርኳሱ ዙሪያ የሚገኙ ለተጫዋቾች በአውሮፓ የሙከራ እድል የሚያመቻቹ ሰዎች ቢኖሩን ብዙ ተጫዋቾች በአውሮፓ የመጫወት እድልን ያገኙ ነበር፡፡”
በሃገር ውስጥ ለተጫዋቾቻችን እየተሰጠ ያለው ስልጠና እድገታቸው እንዲቀጭጭ አድርጎታል፡፡ ከሃገር ውጪ ወጥተው ሲጫወቱ የሚያገኙት ልምድ ግን በአንፃሩ ሲያሻሽላቸው ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ በመጫወትህ እና የስልጠናውን ሁኔታ ስለምታውቅ እንዲሁም አሁን ላይ በሩሲያ ከሶስት ወር በላይ በመቆየትህ ስለዚህ ጉዳይ የተሻለ ግንዛቤ ያለህ እንደመሆኑ ምልከታህ ምንድን ነው?
“አዎ አሁን የምሰራው ልምምድ በጭራሽ ከኢትዮጵያ ጋር ካለው አይገናኝም፡፡ በጣም ይለያያሉ፡፡ እዚህ የሚሰጠን ስልጠና እንደተጫዋች እንድታድግ እና በአጨዋወትህ ለውጥ እንድታመጣ ነው የሚያደረግህ፡፡ በአካል ብቃት የተሻለ ስራ ይሰራሉ፡፡ በዚህ ላይ የተሻለ ስራ ከሰራህ በኳሱ የምትፈልገውን ነገር ለመስራት ይቀልሃል፡፡ በኢትዮጵያ የሚሰጠን ልምምድ በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስልጠናው የሚሰጠን ስለእግርኳሱ በትክክል በተረዱ አሰልጣኞች አለመሆኑ ነው፡፡”
ጋቶች በውድድር ዘመኑ ከአንዚ ጋር ከወራጅ ቀጠናው ከመውጣት ሌላ ምን አቅዷል?
“እቅዴ በዋናው ቡድን የመጫወት እድል እስከማገኝ ድረስ ጠንክሬ መስራት ነው፡፡ አሁን ላይ የዋናው ቡድን አካል ስለሆነኩ እድል ለማግኘት ጠንክሬ ስራዬን መስራት አለብኝ፡፡”