ደደቢት እግርኳስ ክለብ ከጣሊያኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ኤርያ ጋር የሶስት አመታት የትጥቅ አቅርቦት ውል መፈራረሙን ዛሬ በሞናርክ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ተደርጓል፡፡ በቦታውም የማልያ ትውውቅ ተገርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይፋዊ የትጥቅ አቅራቢ የሆነው ኤርያ በክለብ ደረጃ ከኢትዮጵያ ክለብ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስምምነት እንዳደረገ የተገለፀ ሲሆን ግሎባል ስፖርት በተባለ የኤርያ የኢትዮጵያ ወኪል በኩል ስምምነቱ እንደተደረገ ተነግሯል፡፡ ለሶስት አመት በሚቆየው ስምምነትም ለወንዶች እና ለሴቶች ቡድን 100 አንደኛ እና 100 ሁለተኛ መለያዎች በአጠቃላይ 200 መለያዎች በየአመቱ ክለቡ ከኤርያ እንደሚያገኝ ተነግሯል፡፡
ኤርያ ኩባንያን በመወከል ሚስተር ካርሎ ስለ ስምነቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር ስላለን ነው ስራዎችን ለመስራት የተነሳሳነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ይፋዊ ትጥቅ አቅራቢ ከሆንን በኃላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በደንብ የመስራት ፍላጎቱ አድሮብናል፡፡” በማለት ከደደቢት ስፖርት ክለብ ጋር በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ስለ ስምምነቱ ለሚዲያዎች ገለፃ ያደረገ ሲሆን በጥራት ረገድ የተሻለ አቅርቦት እንደሚያቀርቡልን በማመናቸው እና በእቅዳቸው ስለተማረኩ ስምምነቱን እንዳደረጉ ገልፃዋል፡፡ አቶ ሚካኤል ከኩባንያው ጋር የመለያ ስምምነት ብቻ ማድረጋቸው የገለፁ ሲሆን የሌሎች ትጥቆችን አቅርቦት በተመለከተ በኤርያ በኩል ከናይኪ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ለማስመጣት እንዳሰቡ ተናግረዋል፡፡
ክለቡ ለኤርያ የሚከፍለው የገንዘብ መጠን በመግለጫው ላይ በይፋ ያልተነገረ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከቻይና ከሚመጡት መለያዎች አንፃር በዋጋ ረገድ ከፍተኛ ቅናሽ እንደተገኘ ተነግሯል፡፡ በስምምነቱ ላይ የትጥቅ አቅርቦት ብቻ ከኤርያ እንደማያገኙ የገለፁት ደደቢቶች የአሰልጣኞቻቸውን የእውቀት ደረጃ ለማሳደግ አሰልጣኞችን ወደ ውጪ ሃገር በመላክ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚያገኙም ገልፀዋል፡፡ ለደጋፊዎች በመጀመሪያ ዙር 200 ለህፃናት እንዲሁም 800 ለአዋቂዎች በአጠቃላይ 1000 የሚሆን መለያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነ እና በቅርብ ቀን ለገበያ እንደሚቀርብ የተነገረ ሲሆን ይህንን ቁጥር ግን በቀጣይ ለማሳደግ ስራዎች እንደሚሰሩ ተነግሯል፡፡