​የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ አመታዊ ስብሰባ እና የ2009 እጣ ማውጣት ስነስርአት ተካሄደ

የ2009 የ1ኛ ሊግ የክለቦች አመታዊ ስብሰባ እና የ2010 ዓም የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት የክለብ ተወካዮች ባሉበት ዛሬ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ተከናውኗል።

በስብሰባው የተገኙት የኢትየጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለክለቦቹ ምስጋና አቅርበዋል። “በዝቅተኛ መሰረተ ልማት ውድድር ላይ መሳተፋችሁ ትልቅ ምስጋና የሚያስችራችሁ ነው። በሃገሪቱ ላይ የሚከናወኑ የእግር ኳስ እንቅስቃሴዎች መሰረቱ እናንተ በመሆናችሁ ከፍተኛ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል።” ብለዋል።

ከመክፈቻ ንግግሩ በኃላ የተለያዩ ኮሚቴዎች የ2009 የስራ አፈፀፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የሊግ ኮሚቴውን ሪፖርት አቶ የሽዋስ በቀለ በቅድሚያ አቅርበዋል። 56 ክለቦች በ 5 ምድብ ተከፍለው በተወዳደሩበት የ1ኛ ሊግ ከ1400 በላይ ተጫዋቾች የተሳተፉ ሲሆን በአመቱ ላይ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ላይ ነጥቦች ተነስተው ገለፃ ተደርጎባቸዋል። የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች፣ የመወዳደሪያ ሜዳዎች ለጨዋታ ምቹ አለመሆን፣ የዳኝነት ውሳኔዎችን በፀጋ አለመቀበል እና ሌሎችም በአመቱ ላይ የታዩ ችግሮች እንደነበሩ የተነገረ ሲሆን በቀጣይ እነዚህን ችግሮችን ለመቅረፍ ስራዎች እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።


አቶ በቀለ አበራ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በአመቱ የተሰሩ ስራዎችን ገለፃ አድርገዋል። ለ574 ጨዋታዎች 574 ዋና፣ 1148 ረዳት፣ 574 አራተኛ ዳኞች ምዝገባ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ከተመዘገቡት ዳኞች እንደ ጨዋታው ክብደት እና በየጨዋታዎቹ ላይ ከሚያሳዩት ብቃት አንፃር ምደባዎች እንደተደረጉ በሪፖርቱ ተገልፃል፡፡
የፀጥታ እና ስነ ምግባር ኮሚቴ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በተመሳሳይ የአመቱን የውድድር አፈፃፀም ሪፖርት ለክለብ ተወካዮች ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱ ላይም የክለብ ተወካዮች ውይይት አድርገውበታል።

ለረጅም ሰአት ከቆየው የክለቦች እና የአወዳዳሪው አካል ውይይት በኋላ የ2010 የውድድር ደንብ እነና እጣ ማውጣት ስነስርአት የተደረገ ሲሆን አንዳንድ ደንቦች ላይም ከአምናው ለውጥ ተደርጎባቸዋል፡፡

-በዘንድሮው ውድድር የየምድባቸውን ግርጌ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች ወደየክልላቸው  ሊጎች ይወርዳሉ፡፡

-አምና ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያልፉበት መንገድ ዘንድሮ የተቀየረ ሲሆን ከየምድቡ ከ1-3 የሚወጡ 15 ክለቦች እና ጥሩ 4ኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቅ አንድ ቡድን በድምሩ 16 ቡድኖች በአንድ የተመረጠ ከተማ የማጠቃለያ ጨዋታ አድርገው 6 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊጉ ያድጋሉ፡፡

-በዘንድሮ ውድድር ላይ 65 ክለቦች ሲካፈሉ 49 ነባር፣ 6 ከከፍተኛ ሊግ የወረዱ፣ 8 ከክልል ክለቦች ሻምፒዮና ያደጉ ናቸው፡፡ 2 ክለቦች (የቤንሻንጉሉ ንስር እና የአፋሩ ካድባ አፋር) የክልሎቹን እግርኳስ ለማነቃቃት በሚል በስራ አስፈጻሚው ውሳኔ ወደ ሊጉ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

-ውድድሩ ይጀመራል ከተባለበት ጥቅምት 18 ከአንድ ወር በላይ ተገፍቶ ህዳር 25 ይጀመራል ተብሏል፡፡


ተሳታፊ ክለቦች
የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦች

ምድብ ሀ

ቱሉ ቦሎ ከተማ፣ አምቦ ከተማ፣ ወሊሶ ከተማ፣ አሶሳ ከተማ፣ ሆለታ ከተማ፣ መቱ ከተማ፣ ጋምቤላ ከተማ፣ ጋምቤላ ዩኒቲ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ነቀምት ከተማ፣ ዱከም ከተማ፣ ነስር ክለብ

ምድብ ለ

ሞጆ ከተማ፣ ባቱ ከተማ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ መተሀራ ስኳር፣ ቢሾፍቱ ከተማ፣ ገላን ከተማ፣ ሐረር ሲቲ፣ ወንጂ ስኳር፣ ካሊ ጅግጅጋ፣ ኢትዮ ሶማሌ ፖሊስ፣ ሐረር አባድር፣ ድሬዳዋ ኮተን፣ ካድባ አፋር

ምድብ ሐ

ዳባት ከተማ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ አማራ ፖሊስ፣ ደባርቅ ከተማ፣ ሰሎዳ አድዋ፣ ራያ አዘቦ፣ ትግራይ ውሃ ስራ፣ ትግራይ ዋልታ ፖሊስ፣ አዊ አምፒልታቅ፣ ላስታ ላሊበላ፣ ዳሞት ከተማ፣ የጁ ፍሬ ወልዲያ፣ መርሳ ከተማ፣ ሰሜንሸዋ ደብረብርሀን

ምድብ መ

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ፣ ልደታ ክ/ከተማ፣ ቂርቆስ ክ/ከተማ፣ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ፣ ጨፌ ዶንሳ፣ ለገጣፎ 01፣ ቦሌ ክ/ከተማ፣ ቦሌ ገርጂ ዩንየን፣ ጎጃም ደብረማርቆስ፣ ጉለሌ ክፍለከተማ፣ ናኖ ሁርቡ፣ ሰንዳፋ በኬ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ

ምድብ ሠ

ጋሞ ጨንቻ፣ ሮቤ ከተማ፣ ኮንሶ ኒውዮርክ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ቡሌ ሆራ ከተማ፣ ሀዲያ ሌሙ፣ ጎባ ከተማ፣ ጂንካ ከተማ፣ አርሲ ነገሌ፣ ሺንሺቾ ከተማ፣ ጎፋ ባሪንቼ፣ ጋርዱላ ከተማ

የውድድሩን ፕሮግራም በሌላ ዘገባ ይዘን እንቀርባለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *