የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በሁለት ጨዋታዎች ተጀመረ

በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ዘንድሮ ለ12 ጊዜ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ዋንጫ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ ከምድብ አንድ በተደረጉ ጨዋታዎች አዲስ አበባ ከተማ ደደቢትን 1 ለ 0 ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ያለግብ አቻ ተለያይተዋል ።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የደደቢት እና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ደደቢቶች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል ። የአዲስ አበባ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እምብዛም ያላስቸገራቸው ሰማያዊ ለባሾቹ በሽመክት ጉግሳ እና ፋሲካ አስፋው ያደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን መጠበቅ ባይችሉም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጫና ፈጥረው ስለመጫወታቸው ማስራጃዎች ነበሩ ።  ከዚህ በተጨማሪም የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ቡድን በአለምአንተ ካሳ አማካይነት ከግቡ አፋፍ ላይ ያገኘውንን ዕድል ያመከነ ሲሆን ብርሀኑ ቦጋለ አስቆጥሮት የነበረው የቅጣት ምት ጎልም ሊሻርበት ችሏል ።  ቡድኑም ብልጫ በወሰደበት እና በተደጋጋሚ ወደጎል በተጠጋበት በነዚህ ደቂቃዎች ያገኛቸው ዕድሎች ኢላማቸውን የጠበቁ እና ፍሬያማ እንዲሆኑ ማድረግ አለመቻሉ ዋጋ አስከፍሎታል ።

ሁለተኛውን አጋማሽ የቅርፅ ለውጥ በማድረግ እና አዲስ ፈራሚውን ሙሴ እንዳለን ቀይረው በማስገባት የጀመሩት አዲስ አበባዎች በተለይም በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ የበላይነት ማሳየት ችለዋል ። በፈጠሩትም ጫና በርካታ የቆሙ ኳስ ዕድሎችን ሲፈጥሩ በፊት አጥቂው ፍቃዱ አለሙ እና ሙሴ እንዳለ አማካይነት ጠንካራ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ። 56ኛው ደቂቃ ላይም ዳዊት ማሞ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ በመጠቀም እንዳለማው ታደሰ ለቀያዮቹ የማሸነፊያዋን ጎል ማስቆጠር ችሏል ። 

ከጎሏ መገኘት በኃላ ቀስ በቀስ ወደኃላ በማፈግፈግ የነበራቸውን የማጥቃት የበላይነት እያጡ የመጡት አዲስ አበባዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ደደቢቶች በርካታ የግብ ዕድል እንዲፈጥሩ በር ከፍተዋል ። ሆኖም ደደቢቶች ብርሀኑ ቦጋለ 82ተኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ከሞከረው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ውጪ ያገኟቸውን ግልፅ አጋጣሚዎች አቤል እንዳለ እና ፋሲካ አስፋው ሳይጠቀሙባቸው በመቅረታቸው ግብ ሳያገኙ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአሰልጣኝ አስራት አባተ ቡድን ውስጥ አምና ከግራ መስመር በመነሳት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የምናውቀው እና በዕለቱ ጨዋታ ላይ በጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ጥሩ የተንቀሳቀሰው እንዲሁም ለብቸኛዋ ጎል መገኘት ምክንያት የነበረው  ዳዊት ማሞ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ መመረጥ ችሏል ።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በደጋፊዬቻቸው ከዎትሮው የተለየ ድምቀት ታጅበው ወደሜዳ ይገቡትን ኢትዮጵያ ቡናዎችን በርካታ አዳዲስ ፈራሚዎቻቸው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ካስገቡት ጅማ አባጅፋሮች ጋር አገናኝቷል ። የመጀመሪያው አርባ አምስትም መልካም እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ ሲያልፍ ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራ የተሻለው ሆነው ታይተዋል ። በተለይም የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የነበረችው የክሪዚስቶም ንታንቢ የቅጣት ምት እና ከ5 ደቂቃዎች በኃላ ኤልያስ ማሞ ከረጅም ርቀት የሞከረው ኳስ እንደ አዲሱ ያባጅፋር ግብ ጠባቂ ዳንኤል ኦጄ ምርጥ ብቃት ባይሆን ኖሮ ግብ ሊያስገኙ ሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ ። አባ ጅፋሮች በበኩላቸው የተወሰደባቸውን የኳስ ብልጫ መሀል ሜዳ ላይ በማርገብ እና አልፎ አልፎ ወደግብ በመድረስ ጥሩ ተንቃስቀሰዋል ። በተለይም የቀኝ መስመር አማካዩ እንዳለ ደባልቄ በግሉ የኢትዮጵያ ቡናን የተከላካይ መስመር ሚረብሽ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን 36ኛው ደቂቃ ላይም ኢላማዋን የጠበቀች አስደናቂ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር ።

ሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታ ፍጥነትም ሆነ በግብ ሙከራዎች ብዛት ይበልጥ የተሻለ ሆኖ ታይቷል ። እንደመጀመሪያው ሁሉ  ኢትዮጵያ ቡና ብልጫውን ወስዶ ጨዋታውን ቢጨርስም የግብ ሙከራ በማድረግ ግን ቀዳሚ የነበሩት አባ ጅፋሮች ነበሩ ። ሆኖም የአሰልጣኝ ገ/መድህን ስብስብ ሌላ ሙከራ ለማግኘት እስከ 75ኛድ ደቂቃ ድረስ ለመቆየት ተገዷል ። ሁለቱም አጋጣሚዎች ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ በእንዳለ ደባልቄ ጠንካራ ምቶች የተገኙ ነበሩ ። ከዚህ ውጪ ጅማዎች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቡና የግብ ክልል ለመግባት ያደርጉ ከነበረው ጥረት ውጪ ጥርት ያለ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም ። ከዛ ይልቅ ከወገብ በታች የነበራቸው ጥንካሬ የተወሰደባቸውን ብልጫ ተቆጣጥረው ለመውጣት አግዟቸዋል ። ተጨዋቾቻቸውን ለመመዝን አጋጣሚውን ለመጠቀም በሚመስል መልኩ አምስት የተጨዋች ቅያሪዎችን ያደረጉት ቡናዎች በርካታ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል ። ሆኖም አብዛኞቹ አጋጣሚዎች  ከጅማዎች ሳጥን አካባቢ ይጨናገፉ የነበረ ሲሆን የተፈጠሩት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችም በዳንኤል አጃዬ አማካይነት ከሽፈዋል ። በተለይም 45ኛው እና 69ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ በጥሩ የማጥቃት ፍሰት ከግብ አፋፍ ቢደርስም ሳሙኤል ሳኑሚ አጋጣሚዎቹን ወደ ግብ ሳይቀይራቸው ቀርቷል ። በዚህም መልኩ ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል ።

አምና በጅማ አባ ቡና የአማካይ ክፍል ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖውን ያሳረፈው ዩጋንዳዊው  አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ፈራሚ ክሪዚስቶም ንታንቢ በሳየው እንቅስቃሴ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *