የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት ራባት ላይ ከሞሮኮ የቻን ብሄራዊ ቡድን ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 4-0 ተሸንፏል፡፡
የሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን ለኢትዮጵያ ባቀረበው የወዳጅነት ጨዋታ ግብዣ መሰረት ማክሰኞ ይደረጋል የተባለው ጨዋታ ባልታወቀ ምክንያት ዛሬ ተካሂዷል፡፡ ወደ ጋቦሮኒ አቅንቶ በቦትስዋና የተሸነፈው ብሄራዊ ቡድኑ ከሰኔ ወር ጀምሮ በሁሉም ውድድሮች ካደረጋቸው ጨዋታዎች 8 ጨዋታዎች በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ማሸነፍ የቻለው 1 ጨዋታ (ጅቡቲ) ብቻ ነው፡፡
ሞሮኮ እና ዋሊያዎቹ ባደረጉት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሞሮኮ 3-0 መምራት ስትችል ከእረፍት መልስ 1 ግብ አክላ ማሸነፍ ችላለች፡፡ በጨዋታው ላይ የፊት መስመር ተሰላፊው ጌታነህ ከበደ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ በጨዋታው ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ ተጫዋቾቹን ከተፈጥሯዊ ቦታቸው በመቀየር ሞክረዋል፡፡ ለዚህ ማሳያው የመስመር አጥቂ የሆነው አዲስ ግደይ ባዬ ገዛኸኝን ቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኃላ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ተጫውቷል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ ወደ ራባት ያቀናው 15 ተጫዋቾችን ብቻ ይዞ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ ግብ ጠባቂዎች ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡ ቡድኑ በሐምሌ ወር ጅቡቲን በቻን ማጣሪያ 5-1 ያሸነፈበት ውጤት ብቻ ነው ድል ሆኖ የተመዘገበው፡፡ በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች 4 ሲሸነፍ 3 አቻ ተለያይቷል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ ከሰኔ ወር ጀምሮ ያስመዘገባቸው ውጤቶች እነዚህን ይመስላሉ
ኢትዮጵያ 0-0 ዩጋንዳ (የወዳጅነት)
ጋና 5-0 ኢትዮጵያ (የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ)
ጅቡቲ 1-5 ኢትዮጵያ (የቻን ማጣሪያ)
ዛምቢያ 0-0 ኢትዮጵያ (የወዳጅነት)
ኢትዮጵያ 1-1 ሱዳን (የቻን ማጣሪያ)
ሱዳን 1-0 ኢትዮጵያ (የቻን ማጣሪያ)
ቦትስዋና 2-0 ኢትዮጵያ (ወዳጅነት)
ሞሮኮ 4-0 ኢትዮጵያ (የወዳጅነት)
የኢትዮጵያ ቋሚ አሰላለፍ ከሞሮኮ ጋር ይህንን ይመስላል፡፡ (በቅንፍ የተጠቀሱት ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ናቸው)
ጀማል ጣሰው (ለዓለም ብርሃኑ)
አንተነህ ተስፋዬ (አብዱልራህማን ሙባረክ)፣ ሙጂብ ቃሲም፣ አስቻለው ታመነ፣ ደስታ ዮሃንስ
ሙሉዓለም መስፍን፣ ምንተስኖት አዳነ
ዳዋ ሆጤሳ፣ ፍሬው ሰለሞን (ሳሙኤል ሳሊሶ)፣ ባዬ ገዛኸኝ (አዲስ ግደይ)
ጌታነህ ከበደ