​ወልዲያ ከተጫዋቾቹ ጋር የነበረው ውዝግብ እልባት አግኝቷል

አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመውና ከ13 በላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ወልዲያ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል አራቱ ከክለቡ ጋር የነበራቸውን ልዩነት መፍታታቸው ታውቋል፡፡

በዝውውር መስኮቱ ወደ ክለቡ ከመጡ አራት ተጨዋቾች መካከል ፍፁም ገ/ማርያም ፣ ብሩክ ቀልቦሬ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ምንያህል ተሾመ አስቀድሞ ከስምምነት የደረስነው ክፍያ መፈፀም ሲገባው አልተፈፀመም በማለት በተፈጠረው ውዝግብ ዝግጅት ከጀመሩ በኋላ ማቋረጣቸው ይታወቃል። ሆኖም በክለቡና በተጨዋቾቹ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ  እልባት አግኝቶ ከአራቱ ተጫዋቾች ሦስቱ  ወደ ወልዲያ በማቅናት ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ልምምድ እንደጀመሩ የተሰማ ሲሆን ከኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡደን ጋር ወደ ሞሮኮ ያቀናው ብሩክ ቃልቦሬ ከብሔራዊ ቡድን መልስ ከቡድኑ ጋር የሚቀላቀል ይሆናል፡፡

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ሊጀመር ከአንድ ወር ያነሰ እድሜ በቀረው በአሁኑ ወቅት በተጫዋቾቹና በክለቡ መካከል የተፈጠረው ችግር መቀረፉ ለዋናው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድኑን በተረጋጋ ሁኔታ ለውድድር ለማዘጋጀት እንደ  መልካም ዜና ይወሰዳል።

ወልዲያ በሊጉ የመጀመርያ ሳምንት ጥቅምት 18 መሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማን ያስተናግዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *