12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ “ሀ” ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ደደቢትና ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል፡፡
09:00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ ደደቢት በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ግብ አሽንፎ ወጥቷል፡፡ በጨዋታው ደደቢቶች ባሳለፍነው እሁድ ከተጠቀሙት የቡድን ስብስብ ወስጥ በተከላካይ ስፍራ በሰለሞን ሀብቴ ምትክ አንዶህ ክዊኬን እንዲሁም በአጥቂ አማካዩ አለምአንተ ካሳ ምትክ ሮበን ኦባማን በመተካት በ4-1-3-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ሲጀምሩ በአንጻሩ ጅማ አባጅፋሮች በመጀመሪያው ጨዋታ የተጠቀሙበትን ተመሳሳይ የቡድን ስብስብ ተጠቅመዋል፡፡
በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች በደደቢት በኩል ከሶስቱ አማካዮች ጀርባ በተከላካይ አማካይነት ሚና ወደ ሜዳ የገባው አስራት መገርሳ በጥልቀት ወደ ኃላ በመሳብ ከአራቱ ተከላካዮቹ ፊት በቅርብ ርቀት መጫወቱን ተከትሎ በእሱና ፊት ከሚገኙት ሶስቱ የአጥቂ አማካዮች መካከል ሰፊ ክፍተት በመፈጠሩ ጅማዎች ይህንኑ ክፍተት በመጠቀም በሜዳው ቁመት መካከለኛው ስፍራ ላይ ባደላ መልኩ በርካታ ኳሶችን በመቀባበል በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ነበሩ፡፡ ነገርግን በ13ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች በጅማዎች የግብ ክልል ቀኝ ጠርዝ አካባቢ ያገኙትን የቅጣት ምት የደደቢቱ አምበል ብርሀኑ ቦጋለ በቀጥታ ወደግብ ሲሞክር የጅማው ግብጠባቂ ዳንኤል አጄዬ መትፋቱን ተከትሎ የደደቢቱ የመሀል ተከላካይ ክዌኬ አንዶህ ተንሸራቶ ቡድኑን መሪ ያደረገችውን ግብ ማስገኘት ችሏል፡፡
ሽኩቻ በበዛበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኤፍሬም አሻሞና ጌቱ ረፌራ በጉዳት ተቀይረው ለመውጣት ተገደዋል፡፡
ጅማ አባጅፋሮች በዛሬው ጨዋታ እንደመጀመሪያው ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጠቅጠቅ ብለው በመከላከል እንዲሁም እንደቡድን በጋራ በመሆን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በተደራጀ መልኩ ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በኳስ ቁጥጥር ድርሻ የተሻለ የነበሩት ጅማዎች ሶስቱም የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች በበርካታ አጋሚዎች በተመሳሳይ የሜዳ ክፍል በመገኘታቸው የተነሳ ቡድኑ በሜዳኛው የላይኛው ክፍል ላይ ይፈልገው የነበረውን የፈጠራ አቅም በአግባቡ ከመጠቀም ገድቧቸው ተስተውሏል፡፡
በዚሁ የግብ ሙከራዎች እምብዛም ባልታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በጅማ አባጅፋሮች በኩል እንዳለ ደባልቄ በሁለት አጋጣሚዎች ለሳምሶን ቆሌቻ አመቻችቶ ካቀበላቸውና ሳምሶን ካመከናቸው ኳሶች ውጪ እምብዛም ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎች አልነበሩም፡፡
በዛሬው ጨዋታ በደደቢቶች በኩል ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ማለትም ደስታ ደሙ በቀኝ እንዲሁም ብርሃኑ ቦጋለ በግራ በኩል በአመዛኙ በበርካታ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ በትይዩ ለዝርግ የኃላ አራት ተከላካይነት በቀረበ መልኩ መጫወታቸው ከደደቢት የመስመር አጥቂዎች በጥልቀት ወደ መሀል እያጠበቡ ከመጫወታቸው ጋር ተዳሞሮ ቡድኑ በተጋጣሚ የማጥቃት ወረዳ ውስጥ እንደ ጅማ አይነት ኳስ ሲያጣ ተሰብስቦ የሚከላከል ቡድንን ለማስከፈት በሜዳው አግድመት ቡድኑ ይፈልግ የነበረውን የተለጠጠ የተጫዋቾች እንቅስቃሴን ማግኘት ሳይችል የማጥቃት እንቅስቃሴዎቻቸው በቀላሉ ሲከሽፍ ተስተውሏል፡፡ በአንፃሩ ጅማዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮቻቸው እግር በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች የደደቢትን የመከላከል አደረጃጀት ሲፈትኑ ታይተዋል ፤ ከነዚህም በ48ኛው ደቂቃ ኄኖክ ካሳሁን ከግራ መስመር ወደ መሃል ያሻማውን ተቀይሮ የገባው ተመስገን ገ/ኪዳን ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ በጅማዎች በኩል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡
በጨዋታው ሌላው የታየው አስገራሚ ክስተት የነበረው ባሳለፍነው ሳምንት የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ከግዙፉ የጣሊያን ኩባንያ ከሆነው ኤርያ ጋር ስምምነት የተፈራረሙት ደደቢቶች ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የተቀናቃኝ ትጥቅ አምራች ኩባንያ የሆነው የአዲዳስ ሹራብ ለብሰው ቡድናቸውን ሲመሩ መታየታቸው ነው፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ደደቢቶች በእጃቸው የገባውን መሪነት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ በጥልቀት ወደ ኃላ በመሳብ ሲከላከሉ በአንጻሩ ጅማዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት የተከላካይ መስመራቸውን በእጅጉን ወደ መሀል ሜዳ በማስጠጋት ይበልጥኑ ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡
ጅማ አባጅፋሮች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ እንደማስጠጋታቸው ከፊት የሚገኙት ተጫዋቾች በበቂ ሁኔታ የደደቢት ተጫዋቾች ኳስን እንዳይመሰርቱ ጫና ባለመፍጠራቸው የተነሳ ደደቢቶች ከጅማ ተከላካዮች ጀርባ የሚገኘውን ሰፊ ክፍተት ከተከላካዮቻቸው በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም በተደጋጋሚ ግልፅ የሆኑ የማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይም በ66ኛው እንዲሁም 80ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለውና አክዌር ታም ከጅማው በረኛ አጃዬ ጋር 1ለ1 ተገናኝተው ያመከኗቸው ኳሷች በጣም አስቆጪ ነበር፡፡
ጨዋታው በደደቢት የ1-0 አሸናፊ መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢቶች ነጥባቸውን ወደ ሶስት በማሳደግ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያላቸውን እድል ማለምለም ሲችሉ በአንፃሩ ጅማዎች በ1 ነጥብ ለማለፍ በቀይ ጨዋታ ማሸነፍና የሌሎች ቡድኖችን ውጤት ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቀቅ በኃላ ባሳለፍነው ክረምት ድሬዳዋ ከተማን ለቆ ጅማን የተቀላቀለው ሄኖክ አዱኛ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል፡፡
በማስከተል 11:24 ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያ ቡናና የአዲስአበባ ከተማ ጨዋታ በሶስት ፍፁም ቅጣት ምቶች ታጅቦ በኢትዮጵያ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመሪያው ጨዋታ በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርፅ የመሀል ተከላካዮን ትዕግስቱን በቶማስ ስምረቱ ፣ መሀል ክፍል ላይ ኤልያስ ማሞን በሳምሶን ጥላሁን እንዲሁም ፊት መስመር ላይ በረከት ይሳቅንና እያሱ ታምሩን በአስራት ቱንጆና አቡበከር ናስር በመተካት ጨዋታውን ሲጀምሩ አዲስ አበባ ከተማዎች በበኩላቸው ግብጠባቂው ሀብቶም ቢሰጠኝን በፍሬው ጌታሁን እንዲሁም ማታይ ሎል ፣ ጊት ጋት እና ገናናው ረጋሳን በአዲስ መልኩ ወደ ቡድናቸው በማካተት በ3-5-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡
ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም የመጀመሪያ የግብ ሙከራን በ5ኛው ደቂቃ ማድረግ ችለዋል፡፡ ክሪዚስቶም ንታንቢ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሶስት የአዲስአበባ ተጫዋቾችን አልፎ ወደ አዲስ አበባዎች የግብ ክልል ከገባ በኃላ ወደ መሀል ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ናስር ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ መስኡድ በድጋሚ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረ፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ በነበሩት የመጀመሪያው አጋማሽ ንታምቢ እንደመጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ የቡድኑን የኳስ ስርጭትን በመቆጣጠር እንዲሁም የቡድኑን እንቅስቃሴ በማደረጀት በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡
በ21ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ሳሙኤል ሳኑሚ የአዲስ አበባ ከተማን ተከላካዮች አልፎ ወደ ግብ ለመሄድ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ፋሲል ጌታቸው በሰራበት ጥፋት ቡናዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳሙኤል ሳኑሚ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡
በመከላከል ላይ ተጠምደው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ወደ ኢትዮጵያ የቡና የግብ ክፍል ተጠግተው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ተስተውሏል፡፡ ሆኖም በ38ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ አካባቢ ያገኙትን የቅጣት ምት ተጠቅመው በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን ተጫዋች ገናናው ረጋሳ አማካይነት የአቻነቷን ግብ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ለግቧ መቆጠር የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች የትኩረት ማጣት ዋነኛ መንስኤ ነበር፡፡
በጨዋታው በ3 የመሀል ተከላካዮች ለመጠቀም ያሰቡት አዲስአበባ ከተማዎች ከእነሱ ፊት ከነበሩት አምስት አማካዮች ውስጥ በቀኝ የመስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ተፈጥሮአዊ የመሀል ተከላካይ የሆነው ማታይ ሎል ቦታው የሚጠይቀውን በመከላከል እና ማጥቃት ላይ የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ በበርካታ አጋጣሚዎች ኳስ ለማስጣል ወደፊት ከሄደ በኃላ ከጀርባው የሚኖረውን ሰፊ ክፍተቶችን ተመልሶ ለመዝጋት ሲቸገር ተስተውሏል ፤ እንደውም የኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ሮቤል አስራት በጨዋታው እምብዛም በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የመሳተፍ ተነሳሽነት ባለማሳየቱ የተነሳ ሳይጋለጥ ቀረ እንጂ ክፍተተቱ በጎልህ ሲስተዋል ነበር፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በጥልቀት ወደ መሀል እየተሳቡ ኳሶችን ለመቀባበል ሲሞክሩ ሶስቱ የአዲስ አበባ ከተማ የመሀል ተከላካዮች ከሳሙኤል ሳኑሚ ጋር 3ለ1 በመሆን ጊዜያቸውን በማጥፋታቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በመሀል ሜዳ ላይ የነበራቸውን የሁለት ተጫዋቾችን የቁጥር ብልጫን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ኢትዮጵያ ቡናዎች አስራት ቱንጆን አስወጥተው እያሱ ታምሩን በመተካት በ4-4-2 ዳይመንድ ቅርፅ ሁለተኛውን አጋማሽ መጫወት ችለዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ላይ በሜዳው ላይ ይታይ ከነበረው እንቅስቃሴ በተሻለ በሜዳው እንደወትሮው ሁሉ በርከት ብለው የተገኙት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ያሳዮት ልዩ የሆነ የመብራት ትርኢት ነበር፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ያለ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ58ኛው እንዲሁም በ86ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ሳሙኤል ሳኑሚ ላይ ጊት ጋት በሰራቸው ጥፋቶች የተገኙትን የፍጹም ቅጣት ምቶች ራሱ ሳሙኤል ሳኑሚ በመምታት አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል፡፡ ከሶስተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ ሳሙኤል ሳኑሚ ባጋጠመው ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች በቀሩበት ወቅት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ወንድይፍራው ጌታሁን በግምት ከ40 ሜትር ርቀት ከሚሆን ርቀት ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን የቅጣት ምት የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን የግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በቀጥታ በመምታት ማራኪ ግብን የሆነች የማሳረጊያ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ 4-1 እንዲያሸንፍ አስችሏል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሳሙኤል ሳኑሚ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀለትን ዋንጫ ተረክቧል፡፡