በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው እለት አራት አዳዲስ ተጫዋቾች ማስፈረሙን ክለቡ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል፡፡
ከፈረሙት ተጫዋቾች መካከል በ2008 ክረምት ወደ አአ ከተማ አቅንታ የነበረችው አማካይዋ ቱቱ በላይ ከአንድ አመት የአዲስ አበባ ከተማ ቆይታ በኃላ ዳግም የቀድሞ ክለቧን ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለች ሲሆን ከሷ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይ የነበረችው ቤዛዊት ተስፋዬና የቡድን አጋሯ የነበረችው ተከላካይዋ እታፈራሁ አድርሴ በተመሳሳይ ለክለቡ ለአንድ አመት ለመጫወት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ ከሶስቱ ተጫዋቾች በተለየ የቀድሞዋ የብሔራዊ ቡድን ድንቅ አማካይ ሰሚራ ከማል ከረጅም ጊዜያት ወደ ጨዋታ በመመለስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መፈረም አስገራሚ ሆኗል፡፡ ተጫዋቿ ከ2005 ወዲህ በወሊድ ምክንያት ከእግርኳስ ርቃ ቆይታለች፡፡
በሰላም ዘርአይ የሚሰለጥነው ክለቡ በአምናው የውድድር ዘመን ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፉ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋቾች የሆኑትን መሰሉ አበራ፣ ሂሩት ደምሴ እና አበዛሽ ሚጌሶን ውል ማደሱን አስታውቋል፡፡ በቀጣይም ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቆረብ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ያስፈርማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡