በዝውውር መስኮቱ ኤሌክትሪክ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ ነው

ኤሌክትሪክ በተጫዋቾች ዝውውር ተጠምዷል፡፡ እስካሁን ከ5 ተጫዋቾች ጋር ሲስማማ የ7 ተጫዋቾችንም ውል አድሷል፡፡

ኤሌክትሪክ ለማስፈረም ከተስማማቸው ተጫዋቾች መካከል የንግድ ባንኩ የግራ መስመር ተከላካይ አለምነህ ግርማ የመጀመርያው ተጫዋች ሲሆን 1.1 ሚልዮን ብር ለ2 አመት ሊከፈለው መስማማመቱ ተነግሯል፡፡

የወላይታ ድቻዎቹ ተስፋዬ መላኩ እና አማካዩ አሸናፊ ሽብሩ ሌሎች ለኤሌክትሪክ ለመፈረም የተስማሙ ተጫዋቾች ሲሆኑ ለተከላካዩ 1.1 ሚልዮን ለአሸናፊ ደግሞ 1.2 ሚልዮን ብር ለመክፈል መስማማቱ ታውቋል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ የምናውቀው ሃብታሙ መንገሻም ከኤሌክትሪክ ጋር ከስምምነት ላይ የደረሰ ተጫዋች ነው፡፡ በዳሽን ቢራ የአንድ አመት ቀሪ ኮንትራት የነበረው ሃብታሙ ከክለቡ ጋር ያለውን ውል አፍርሶ ለኤሌክትሪክ ለመፈረም መስማማቱ ተወርቷል፡፡ ለ2 አመትም 1.1 ሚልዮን ሊከፈለው ተስማምቷል፡፡

የሲዳማ ቡናው የመስመር አጥቂ ብሩክ አየለ ከኤሌክትሪክ ጋር መስማማቱም ታውቋል፡፡ ብሩክ ለኤሌክትሪክ ለመጫወት የ2 አመት 1.25 ሚልዮን ብር ይከፈለዋል ተብሏል፡፡

ኤሌክትሪክ እስካሁን የ7 ነባር ተጫዋቾቹን ኮንትራት ሲያራዝም አወት ገ/መድህን ፣ አዲስ ነጋሽ ፣ በኃይሉ ተሸገር ፣ ገመቹ በቀለ ፣ በረከት ተሰማ ፣ አሳልፈው መኮንን እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ውላቸውን ለ2 አመት ያደሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ለተጫዋቾቹ የውል ማደሻም ክለቡ ለእያንዳንዳቸው ከ850ሺህ እስከ 1.2 ሚልዮን ብር ወጪ አድርጓል ተብሏል፡፡

ሄይቲያዊው አማካይ ሳውረን ኦልሪሽ ክለቡን ለቆ ወደ ሃገሩ ሲመለስ ሌሎቹ የውጭ ሃገር ተጫዋቾች (ፒተር ፣ ዊልያም ፣ሲሴ እና ማንኮ ክዌሳ) ኮንትራታቸው ባለመጠናቀቁ በክለቡ ይቆያሉ ተብሏል፡፡

በተለያዩ ክለቦች የሚፈለገው ራምኬል ሎክ ከከልቡ ጋር የውል ማደስ ስምምነት እንዳላደረገ ሲታወቅ ተሸመ ኦሼ እና ጌድዮን ታደሰን ጨምሮ 5 ተጫዋቾች ውላቸውን ጨርሰው እስካሁን የኮንትራት ማደስ ጥያቄ አልቀረበላቸውም፡፡

ቡድኑ ለውል ማደሻ እና አዳዲስ ተጫዋቾች ማስፈረምያ ከፍተኛ ገንዘብ ከማውጣቱ ባሻገር በተለያየ የልምድ እና የብቃት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተጫዋቾች ተመሳሳይ ገንዘብ ወጪ ማድረጉ አስገራሚ ሆኗል፡፡

ያጋሩ