ኢትዮጵያ በኮካ ኮላ የፊፋ የሃገራት ደረጃ መንሸራረቷን ቀጥላለች

የዓለምአቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ የወሩ በሚያወጣው ኮካ ኮላ የሃገራት ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ መንሸራተቷን ተያይዘዋለች፡፡ በ10 ዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከወር ወር ወደኃላ መጓዟን የቀጠለችው ኢትዮጵያም በመስከረም ወር ከነበረችበት 7 ደረጃዎችን ወርዳለች፡፡

በወሩ ውስጥ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታን አድርጋ በሁለቱም ምንም ግብ ሳታስቆጥር የተሸነፈችው ኢትዮጵያ  በ175 ነጥብ በ151ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ኢትዮጵያ ካለፈው ወር ከነበረችበት 144ኛ ሰባት ደረጃዎችን ወርዳ ነው 151ኛ ላይ መቀመጥ የቻለችው፡፡ ዋሊያዎቹ ባሳለፍነው ወር በቦትስዋና 2-0 እና በሞሮኮ የቻን ቡድን 4-0 የተሸነፈበት ጨዋታዎች በፊፋ የተመዘገቡ የወዳጅነት ጨዋታዎች ስላልሆኑ በነጥብ አሰጣጡ ላይ አልተካተቱም፡፡ እነዚህ ጨዋታዎች ተካተው ቢሆን ኖሮ ምንአልባትም የቡድኑ ደረጃ ይበልጥ ማሽቆልቆሉ የማይቀር ነበር፡፡

በ1994 (ኢትዮጵያ አቆጣጠር) በፊፋ ደረጃ 155ኛ የተቀመጠች ሲሆን ይህ ደረጃ በሃገሪቱ ታሪክ መጥፎ የሚባለው ደረጃ ነበር፡፡ ቢሆንም አሁን ላይ ያለንበት ደረጃ ከ1994ቱ ቀጥሎ ዝቅተኛው ሆኖ ተቀምጧል፡፡ የፊፋ የሃገራት ደረጃ በብዙዎች ዘንድ አጠያያቂ ጉዳዮች ቢኖሩትም እንደኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ደረጃ ማሻሻል ልክ እግርኳሱ እንዳደገ ተደርጎ ሲቆጠር ማየት የተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሃገራት ደረጃ 45 ደረጃ ላይ ስትገኝ የምትበልጣቸው የአፍሪካ ሃገራት ብዛት 8 ብቻ ነው፡፡ ከነዚህ 8 ሃገራት ውስጥ ኤርትራ እና ሶማሊያ በቅርብ ግዜያት ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ጨዋታ አለማድረጋቸውን ተከትሎ ነጥብ የላቸውም፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆኑት ጋና ከአፍሪካ 8ኛ ከዓለም 52ኛ፣ ሴራ ሊዮን ከአፍሪካ 23ኛ ከዓለም 99ኛ እንዲሁም ኬንያ ከአፍሪካ 25ኛ እንዲሁም ከዓለም 102ኛ ናቸው፡፡ በአፍሪካ እግርኳስ ካርታ ላይ እምብዛም የማናያቸው እንደስዋዚላንድ፣ ሌሶቶ፣ ኒጀር እና ቻድ ያሉ የአፍሪካ ሃገራት በደረጃው ኢትዮጵያን ይበልጣሉ፡፡

ቱኒዚያ የአፍሪካ የበላይ መሆን የቻለች ሲሆን 1990 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፈችው ግብፅ ሁለተኛ ሆናለች፡፡ ሴኔጋል፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና የዓለም ዋንጫ ተሳታፊዋ ናይጄሪያ ደግሞ እስከአምስት ያለው ደረጃ ይዘዋል፡፡ ከሴካፋ ዞን አሁንም ዩጋንዳ መሪነቷን በማስጠበቅ ችላች ከአፍሪካ 14ኛ ፣ ከዓለም 70ኛ ደረጃ መቀመጥ ችላለች፡፡ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛኒያ እና ሱዳን ከሴካፋ ዞን ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሀገራት ናቸው፡፡

ጀርመን አሁንም በደረጃው አናት ላይ ስትገኝ ብራዚል፣ ፖርቹጋል፣ አርጀንቲና እና ቤልጂየም እስከአምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የዓለም ደረጃ

1 ጀርመን

2 ብራዚል

3 ፖርቹጋል

4አርጀንቲና

5 ቤልጂየም

6 ፖላንድ

7 ፈረንሳይ

8 ስፔን

9 ቺሊ

10 ፔሩ

 

 

የአፍሪካ ደረጃ (በቅንፍ የተጠቀሰው የዓለም ደረጃቸውን ነው)

1 ቱኒዚያ (28)

2 ግብፅ (30)

3 ሴኔጋል (32)

4 ዲ.ሪ. ኮንጎ (35)

5 ናይጄሪያ (41)

6 ካሜሮን (42)

7 ሞሮኮ (48)

8 ጋና (52)

9 ቡርኪና ፋሶ (55)

10 ኮትዲቯር (61)

.

.

.

45 ኢትዮጵያ (151)

2 Comments

  1. ችግር በተፈጠረ ቁጥር ደረጃ ባሽቆለቆልን ቁጥር አሰልጣኝ እያባረርን በማስታወቂያ አሰልጣኝ እየቀጠርን ምን አይነት ለውጥ ልናመጣ እንችላለን?
    አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን በሁሉም ክለቦች ማየት ስንጀምር አሰልጣኙን ተጠያቂ እናደርጋልን፡፡ በርግጥ የአሰልጣኙ ሀላፊነት ቀላል የሚባል አይደለም ሆኖም በማስታወቂያ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መቅጠራችንን ካላቆምን መፍትሄ አይኖረውም፡፡ ከልማዳዊ ቢሮክራሲ መውጣት ይጠበቅብናል፡፡ የኔ ሃሳብ ነው፡፡

  2. ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንዳየነው እንኳንስ ብሄራዊ ቡድናችን ከ9 ጨዋታዎች በ8 ተሸንፎ 1የጅቡቲን ብ/ቡድን አሸንፎና ከዓለም 151ኛ ደረጃ ከአፍሪካ 45ኛ ደረጃ እንዲወርድ አስደርጎ ቀርቶ ውጤት ከምርጥ ጨዋታዎች ጋር ካልተቀናጀ በአሰልጣኞቹና በፌዴሬሽን አመራሮች ላይ ስር – ነቀል እርምጃዎችን(ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን እስከ መዝጋት ድረስ) ሲወስዱና ለችግሮቻቸው መፍትሄ ነው ያሉትን ሲያደርጉ እናያለን ታድያ ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት ተምዘግዝጋ በታሪኳ ያላጋጠማትን የኋልዮሽ ስትሄድ በግልጽ እየታየ ለምን በፌዴሬሽኑ ዙርያ የማስተካከያ እርምጃ አይወሰድም? ግምገማው አሁን እያስመዘገብን ከሚገኘው ውጤት አንጻር እስከሆነ ድረስ በማን እስከምንሸነፍ ድረስ ነው የሚጠበቀው? ከዓለም ከ151ኛ ከመሆን ሌላ ስንተኛ እስክንሆን ድረስ ነው መፍትሄ የማይፈለገው የሀገር ጉዳይ ከግለሰቦች ክብርና ጥቅም ጋር ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ሊታሰብበት ይገባል ቸር እንሰንብት!!!

Leave a Reply