​አአ ከተማ ዋንጫ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤሌክትሪክ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል

የአአ ከተማ ዋንጫ የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የሚያሻግራቸውን ድል አስመዝግበዋል፡፡

በ9፡00 የተጀመረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ጨዋታ በዝናባማ የአየር ሁኔታ ታጅቦ ከጥቂት ተመልካች ጋር ያለ ግብ በአቻ ወጤት ተፈጽሟል፡፡

በመጀመሪያዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድን የሚጠቀስ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልታየ ሲሀን በ19ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ካሉሻ ሀሰን በግሩም ሁኔታ ለጫላ ቢያሳልፍለትም ጫላ የመከነው እና በ25ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ግብ ጠባቂውን አልፎ  ወደ ጎል የመታው ኳስ ጎል ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ አወት ደርሶ ያወጣው ኳስ በጨዋታው የታዩ የመጀመርያ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ፡


ጨዋታው በተቀዛቀዘ ሁኔታ ቀጥሎ በ38ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ግርማ በግምት 25 ሜትር ላይ አክርሮ የመታው ኳስ በዮሀንስ በዛብህ ሲክሽፍበት 43 ደቂቃ ላይ ጥላሁን ወልዴ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ጫላ ድሪባ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የተሻሉ የግብ ሙራዎችንም ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይ በ49ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው ያሻገረውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ በግሩም ሁኔታ መትቶ የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣበት እና በ70ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ምንይሉ ወንድሙ ሙከራ አድርጎ ዮሐንስ ያዳነበት አንዲሁም በ74ኛው ደቂቃ ላይ አቅሌሲያስ ያሻገረውን ኳስ መስፍን ኪዳኔ ያመከነው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡


ጨዋታው ያለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ የአምናው ቻምፒዮን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ5 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ሲችል ሀሙስ 09:30 ላይ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥም ይሆናል፡፡ የመከላከያው ቴዎድሮስ ታፈሰ ደግሞ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀለትን ሽልማት ተረክቧል፡፡
በ 11፡30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ አዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ ተካሂዶ በፈረሰኞቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


በመጀመርያው አጋማሽ ተጭነው የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጎል ለማስቆጠር የፈጀባቸው ሁለህ ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ኢብራሂማ ፎፋና በግራ በኩል የአዳማ ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ አሜ መሀመድ በግንባሩ በመግጨት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
በ5ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ሳትነካ ወድቀሃል በማለት በፌዴራል ዳኛ ይርጋለም ቢጣ ካርድ ሲመዘዝበት በ20ኛው ደቂቃ ላይ ከ አዳነ ግርማ በረጅሙ የተጣለው ኳስ አብዱልከሪም መሀመድን ከግብ ጠባቂው ጋር ቢያገናኝም ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡


ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስ መስርተው ወደ አዳማ የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባለፉት ጨዋታዎች ላይ እንደታየው ግልፅ የጌብ ማስቆጠር እድል መፍጠር ተስኗቸው የታዩ ሲሆን 2ኛውን ግብ እስኪያስቆጥሩ ድረስም ለረጅም ደቂቃዎች ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡  በ42ኛው ደቂቃ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል የመጣውን ኳስ የእለቱ ኮከብ አሜ መሐመድ አስቆጥሮ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት በማስፋት ነበር የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀው፡፡

ከዕረፍት መልስ አዳማ ከተማ በርከታ የተጫዋች ለውጦችን ያከናወነ ሲሆን ውጤቱን ለመቀልበስም ሙከራ አድርገዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ላይም አዲሱ ፈራሚ አላዛር ፋሲካ ባስቆጠረው ጎል የጎል ልዩነቱን ማጥበብ ችለው ነበር፡፡

ከጎሉ በኋላ የአቻነት ጎል ፍለጋ የተንቀሳቀሱት አዳማዎች በ65ኛው ደቂቃ ላይ በሱራፌል ዳኛቸው እና በ78ኛው ደቂቃ በታፈሰ ተስፋዬ አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም በሮበርት ኦደዶንካራ ጥረት ወደ ግብነት ሳይቀየሩ ቀርተው ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ በ5 ነጥቦች ኤሌክትሪክን ብዙ ጎች ባገባ በልጦ ምድቡን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ ሀሙስ 11:30 በግማሽ ፍጻሜው ጅማ አባ ጅፋርን የሚገጥም ይሆናል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው አሜ መሐመድ የጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀለትን ሽልማት ከአቶ አሊሚራህ መሐመድ እጅ ተቀብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *