​ሀዋሳ ከተማ ሙሉአለም ረጋሳን አስፈርሟል

ሀዋሳ ከተማ ከ2 ወራት በላይ የሙከራ ጊዜ ሰጥቶት የነበረው ሙሉአለም ረጋሳን በአንድ አመት ኮንትራት አስፈርሟል፡፡ ሙሉአለም በክረምቱ ከክለቡ ጋር ያሳለፈ ሲሆን በተለያዩ የአቋም መፈተሻ እና በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ ጥሩ አቋም ማሳየቱን ተከትሎ ቋሚ ኮንትትራት እንደሚቀርብለት ሲጠበቅ ቆይቶ በመጨረሻም ፊርማውን አኑሯል፡፡

በ1989 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከሚጠቀሱ ድንቅ አማካዮች አንዱ መሆን የቻለውና በ1994 የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ሙሉአለም በ2000 ፈረሰኞቹን ከለቀቀ በኋላ በሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን እስከ 2007 ድረስ መጫወት የቻለ ሲሆን ያለፉትን ሁለት አመታት ከእግር ኳስ ርቆ ቆይቷል፡፡

ሙሉአለም ለረጅም ጊዜ ከእግርኳስ እንደመራቁ የተጫዋቹ ለሙከራ ክለቡን መቀላቀል እና አሁን ደግሞ መፈረም የስፖርት ቤተሰቡን ለሁለት ከፍሏል፡፡ ገሚሱ በአሁኑ ወቅት ካለው የተጫዋቾቻችን የአካል ብቃት ደረጃ አንጻር በሊጉ ስለማይፈተን መፈረሙ እምብዛም አነጋጋሪ መሆን አይገባውም ሲሉ ሌሎች ደግሞ ለወጣቶች እድል በመስጠት የሚታወቀው ሀዋሳ የቅርብ ጊዜ መልካም ተግባሩን የሚጣረስ ተግባር እየፈጸመ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ በክለቡ በኩል ግን በሙከራ ጊዜው አመርቂ እንቅስቃሴ እንዳሳየና መፈረሙ ከሜዳ ላይ ቀጥተኛ አገልግሎቱ በላይ ፋይዳ እንዳለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ “ተጫዋቹ ይጠቅመናል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ 17 ታዳጊዎች አሉ፡፡ ከሱ በርካታ ልምድን ያገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግም ለክለባችን አጨዋወት እንደ ሙሉአለም አይነት በሳል ተጫዋቾች ያስፈልጉናል፡፡ ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ 

ሀዋሳ ከተማ በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ ከፍተኛ የተከላካይ ችግር እንደነበረበት የታየ ሲሆን ክፍተቱን ለመሙላትም ተጨማሪ አንድ አይቮሪያዊ ተከላካይ በሁለት ቀናት ውስጥ ለማምጣት ጥረት ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *