12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ቀን መርሃ ግብር ዛሬ ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ ከተማ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት አጠናቀው በተሰጡ የመለያ ምቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በመጪው እሁድ ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል፡፡
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢወስዱም ከወትሮው በተለየ ጥንቃቄን አክለው ወደ ጨዋታው የቀረቡት ጅማ አባጅፉሮች የተሻለ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል እስጠግተው ሲከላከሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሜዳኛው የላይኛው ክፍል የሚገኙት ተጫዋቾች በበቂ ሁኔታ ጫና ማሳደር ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ በረጃጅሙ በሚላኩ ኳሶች የጅማ አጥቂዎች ኳሶችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ጠንካራ በነበረው የቀኝ መስመራቸው በኩል ወደ መሀል ኳሶችን በመጣል የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ችለዋል ፤ በተለይም ሳሙኤል ተስፋዬና አዳነ ግርማ ያመከኗቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ በአንጻሩ ጅማ ከተማዎች በ45ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገ/ኪዳን ሶስት ተጫዋቾችን አልፎ ያቀበለውን ኳስ ዮናስ ገረመው ሞክሮ ለአለም ብርሃኑ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተደረጉ ሙከራዎች በጣም አስቆጭዋ ነበረች፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ደከም ያለ እንቅስቃሴ ታይቶበታል ፤ ጅማ አባጅፋሮች በይበልጥ ወደ ሜዳቸው ሰብሰብ ብለው ሲከላከሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ ከአሜ መሐመድ ቅያሬ በኃላ በይበልጥ በረጃጅሙ በሚላኩ ኳሶች ፍጥነቱን በመጠቀም ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡
በ62ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ዳንኤል አጃዬ በግሩም ሆኔታ ያዳናት ኳስ ስትመለስ በድጋሚ በኃይሉ አሰፋ የጅማ ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ ኳሷን ወደ ግብ ለመላክ ጥረት ሲያደርግ የጅማው ግብጠባቂ በሰራበት ጥፋት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አዳነ ግርማ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በ78ኛው ላይ አበባው ቡጣቆ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት አዳነ ግርማ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢገጨውም ኳሱ ግን ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ 8 ደቂቃ ሲቀረው በስታዲየሙ አቅራቢያ የሚገኝ የኃይል አስተላላፊ ትራንስፎርመር በመፈንዳቱ የስታዲየሙ ፓውዛ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ጨዋታው ለ23 ያክል ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል፡፡
ከ23 ያክል ደቂቃዎች መቋረጥ በኃላ የቀጠለው ጨዋታ ምንም ግቦችን ሳይስተናገድበት 0ለ0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተክትሎ ጨዋታው ወደ መለያ ምት ለማምራት ተገዷል፡፡ በመለያ ምቱም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የመቱት አራቱም ተጫዋቾች ሲያስቆጥሩ በጅማ አባጅፋሮች በኩል ሳምሶን ቆልቻና ኤልያስ አታሮ የመለያ ምታቸውን በማምከናቸው ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የጅማ አባጅፋሩ ዮናስ ገረመው የጨዋታው ኮከብ ሆኖ በመመረጡ የተዘጋጀለትን ሽልማት ከኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እጅ ተረክቧል፡፡