ባንክ ቡድኑን እንደ አዲስ እየገነባ ነው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደቀደመው የዝውውር መስኮት ሁሉ በዘንድሮውም ክረምት የዝውውር መስኮቱ ዋና ተዋናይ እየሆነ ነው፡፡ ቡድኑ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማምጣት ከስምምነት ሲደርስ ኮንትራታቸው የተጠናቀቁ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾቹን ኮንትራት ላለማደስ ወስኗል፡፡

ባንክ ለማስፈረም ከተስማማቸው ተጫዋቾች መካከል የቀድሞው የቡና ተከላካይ ቶክ ጄምስ በትልቅነቱ ቅድሚያውን ይይዛል፡፡ አምና 2ኛውን ግማሽ የውድድር ዘመን በወልድያ ያሳለፈው ቶክ አምና በኣመራጭ ተከላካይ እጦት የተቸገረውን ቡድን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኤሌክትሪኩ አማካይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ሌላው ለቡድኑ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ ተጫዋቹ ከባንክ ጋር የተስማማው በቃል ደረጃ እንደሆነና የተሻለ ገንዘብ ላቀረበለት ኤሌክትሪክ ውሉን ለማደስ በ1.3 ሚልዮን ብር እንደተስማማም ተነግሯል፡፡ ተጫዋቹ ዛሬ የትኛውን ክለብ እንደሚመርጥ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቡድኑ ለማስፈረም ከስምምነት ላይ የደረሳቸው ሌሎቹ 4 ተጫዋቾች በሙሉ ከአዳማ ከነማ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ግብ ጠባቂው ፌቮ ኢማኑኤል ፣ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አንተነህ ገ/ክርስቶስ ፣ አማካዩ አምሃ በለጠ እንዲሁም አጥቂው ዳኛቸው በቀለ አዳማ ከነማን ለቀው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በቡድኑ ውስጥ ኮንትራታቸው የተጠናቀቁ 17 ተጫዋቾች ያሉ ሲሆን ክለቡ ኮንትራታቸውን ያደሰላቸው ተጫዋቾች ግን 5 ብቻ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ለከርሞ አዲስ ቡድን እያዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ አሁን በቡድኑ ውስጥ ኮንትራታቸው ከተጠናቀቁት ውስጥ የምንፈልጋቸው 6 ያህሉን ነበር፡፡ አምስቱን ለማራዘም የተስማማን ሲሆን አንዱ (ደረጄ መንግስቱ) በበጀት ምክንያት እስካሁን አላራዘምንለትም፡፡ በርካታ ተጫዋቾች ለቀን አዳዲስ ተጫዋቾች የምንይዝ በመሆኑ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን አዲስ ቡድን ነው የምንሰራው›› ብለዋል፡፡

ባንክ ኮንትራታቸውን ያደሰላቸው ተጫዋቾች ተከላካዮቹ ቢንያም ሲራጅ ፣ አቤል አበበ ፣ አዲሱ ሰይፉ እና ዳንኤል አድሃኖም እንዲሁም አምበሉ ታድዮስ ወልዴ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 12 ተጫዋቾች ኮንትራታቸው የመታድስ እድላቸው ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡ የግራ መስር ተከላካዩ አለምነህ ግርማ ባንክን ለቆ ወደ ኤሌክትሪክ ማምራቱ የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ከመግባቱ በፊት ለባንክ ለ2 አመታት የተጫወተው ቢንያም አሰፋ ከክለቡ ጋር ግኙነት ቢጀምርም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ኮንትራቱን ለማደስ በድርድር ላይ በመሆኑ የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡

አምና የክለቡ ከፍተኛ ግብ አግቢ የነበረው ፊሊፕ ዳውዚ በግብፅ የሙከራ ጊዜ አሳልፎ ሳይሳካለት ወደ ኢትዮጵያ መመለሱና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች ሆኖ እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡

ያጋሩ