​አፍሪካ| ማሊ በታዳጊዎች የዓለም ዋንጫ ግስጋሴዋን ቀጥላለች

የፊፋ የዓለም ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ በህንድ አስተናጋጅነት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ አፍሪካ በአራት ሃገራት በውድድሩ ላይ የተወከለች ሲሆን ማሊ፣ ጋና እና ኒጀር ከምድባቸው ማለፍ ሲችሉ ጊኒ ከምድብ በግዜ መሰናበቷ ይታወሳል፡፡ በሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ በአፍሪካ የወጣቶች እግርኳስ ታላቅ ስም የገነቡትን ማሊ እና ጋናን አገናኝቶ የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ማሊ 2-1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አምርታለች፡፡

በኢንድራ ጋንዲ አትሌቲክ ስታዲየም በተደረገው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ማሊዎች በተለይም በመሃል ሜዳ የነበራቸው የጨዋታ ብልጫ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል እንዲቀርቡ አስችሏቸዋል፡፡ በጨዋታው ወቅት በስታዲየሙ ይጥል የነበረውን ዝናብ ተከትሎ የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ አመቺ አለመሆኑ በተለይ የጋና ተጫዋቾች ጨዋታው ይበልጥ ፈታኝ እንዲሆንባቸው አድርጓል፡፡ ማሊ ተጭና መጫወቷን ተከትሎ በላሳና ንዳዬ አማካኝነት ያልተሳካ የግብ እድ መፍጠር ችላለች፡፡ ሃጂ ድራሜ በጋና የግብ ክልል ውስጥ ያገኘውን እድል በአግባቡ ተጠቅሞ ማሊ በ15ኛው ደቂቃ መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ጋና ውሃ ባዘለው ሜዳ ለመጫወት እየፈተናት እንዲሁም ማሊ ሁኔታውን ተቋቁሞ በመጫወት የመጀመሪያውን አጋማሽ አገባደዋል፡፡

በሁለተኛው 45 የጋናው ግብ ጠባቂ ዳንላድ ኢብራሂም ከአደጋ ክልሉ ወጥቶ ኳስን ለማራቅ በሚሞክረበት ቅፅበት የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ጀሙሳ ትራኦሬ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ በንፅፅር ጋናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሳዲቅ ኢብራሂም ላይ ፎዴ ኮናቴ የሰራውን ጠፋት ተከትሎ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት ኩዱስ መሃመድ ከመረብ አዋህዶ ጋናዎች ውጤቱን ቢያጠቡም ከመሸነፍ ግን ሊድኑ አልቻሉም፡፡ ቢሆን በተለይ በመጨረሻዎቺ 20 ደቂቃዎች ውስጥ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጋናዎች ከማሊ በተሻለ ብልጫን ወስደው ተጫውተዋል፡፡ ሃገራቱ በስድስት ወራት ውስጥ ሲገናኙ ይህ ለሶስተኛ ግዜ ሲሆን ማሊ በሁሉም ጨዋታዎች ጋና ላይ ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ጨዋታው አመቺ ባልነበረ ሜዳ እና በዝናብ ታጅቦ መካሄዱን ተከትሎ የጋናው አሰልጣኝ ፓ ክዌሲ ፋቢን ጨዋታው መራዘም እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡ በ40ኛው ደቂቃ የተቆጠረ ግብም አሜሪካዊው የመሃል ዳኛ ባልተገባ መልኩ መሻራቸውን አሰልጣኝ ፋቢን ተናግረዋል፡፡


በቶጎዋዊ ጆናስ ኮምላ የምትመራው ማሊ በታዳጊዎች እግርኳስ ስኬታማነቷን ቀጥላለች፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ውድድር ቺሊ ላይ በፍፃሜው በናይጄሪያ ተሸንፋ ዋንጫ አጥታለች፡፡ ማሊ ምንም እንኳስ ተስጥኦ ያላቸው ወጣቶችን ብትይዝም በአፍሪካ ከተንሰራፋው የእድሜ ማጭበርበር አባዜ ግን መውጣት አልቻለችም፡፡ በታዳጊ ውድድሮች የምታስመዘግበውን ውጤት ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ለማምጣት ስትቸገር እየተስተዋለ ነው፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ኮምላ አዲስ አበባ ላይ በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ውጤት 4-1 ከረቱ በኃላ ለማሊ የታዳጊዎች እግርኳስ መነቃቃት ምክንያት ጀርመናዊውን የአሁኑ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ አማካሪ ዩአኪም ፊከርትን መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በግማሽ ፍፃሜው ማሊ ከስፔን እና ኢራን አሸናፊ ጋር ስትጋጠም ዩናይትድ ስቴትስን 4-1 የረታችው እንግሊዝ ከብራዚል እና ጀርመን አሸናፊ ጋር የምትገናኝ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *