​ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ለ5ኛ ጊዜ አነሳ 

ለ12ኛ ጊዜ ከመስከረም 28 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲካሄድ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ተደምድሟል፡፡ እጅግ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ በነበረውና ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮጵያ ቡና ባገናኘው ተጠባቂው የፍፃሜ ጨዋታ እንደወትሮው ሁሉ የተጠበቀውን ያህል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሳይታይበት በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌደሬሽን ለሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች በውድድሩ ከጅማሮው አንስቶ ላሳዩት እጅግ ማራኪ የአደጋገፍ ስርአት ልዩ ዋንጫ በተወካዮቻቸው በኩል ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሆኖም በጨዋታው መጀመርያ የነበረው መልካም ድባብ ብዙም ሳይዘልቅ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ረብሻ ደጋፊዎች ተጎድተዋል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የጠሩ የግብ እድሎች ሳይታይበት ፤ በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ የሚቆራረጥ እና አሰልቺ እንቅስቃሴ በርክተውበት ተስተውሏል፡፡ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም እንኳን ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ቢሆኑም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ2ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ከቆመ ኳስ ያሻማውና ደጉ ደበበ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ኤልያስ ማሞ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ ከጊዮርጊስ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ አክርሮ በመምታት የሞከረውና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችው ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ፡፡


የመጀመሪያ አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በረጅሙ ወደፊት የላኩትን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ ቶማስ ስምረቱና ግብ ጠባቂው ሀሪሰን ሄሱ ባለመናበብ የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ኢብራሂማ ፎፋና ቡድኑን መሪ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1ለ0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የሚጋሩት በተለምዶ ካታንጋ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ከፀጥታ ሀይሎች ቅድመ ጥንቃቄ መጓደል ጋር ተደማምሮ በሁለቱ ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ደጋፊዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በስፍራው የነበሩት የፀጥታ ሀይሎች ቁጥር ማነስ እና ቸልተኝነትን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭትን ለመቆጣጠርም በርካታ ደቂቃዎች ፈጅቷል፡፡ የእግርካሳችን ደዌ እንደነበረ ሲነገርለት የነበረው የስታዲየሞች ሁከት በጊዜ ሂደት ለውጦች ስለማሳየቱ እየተነገረ በመጣበት በዚህ ጊዜ ዳግም መሰል ሁከት መከሰቱ የችግሩን አሳሳቢነትንና ለውጦች ቢታዩም አሁንም በርካታ ስራ መሠራት አንዳለባቸው የጠቆመ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

በተመሳሳይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ደጋፊዎችን ለማስተባበር የተለየ አንፀባራቂ ልብስን ከለበሱት የደጋፊ አስተባባሪዎች መሃል ሁሉንም ባይወክሉም ጥቂቶች እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ በቀጥታ በሁከቱ ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡


በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ፤ ከነዚህም መካከል ባለፉት ጥቂት አመታት ቀስ በቀስ ከወትሮው በተሻለ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ሜዳ መምጣት የጀመሩት ሴቶች እንዲሁም ህፃናት በዚሁ ሁከት የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ መጀመር ከነበረበት ከግማሽ ሰአት በላይ ዘግይቶ ነበር የተጀመረው፡፡ ወደ ግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ በነበሩበት የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለማጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ትተው የሚሄዱትን ክፍተት በተሻለ ሁኔታ ወደ መስመር ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ስጋት መፍጠር ችለዋል፡፡

ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በካታንጋና ሚስማር ተራ አካባቢ የነበሩ ጥቂት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ውስጥ ድንጋይ በመወርወራቸው የተነሳ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች በድጋሚ ሊቋረጥ ችሏል፡፡

ጨዋታውም ምንም አይነት ተጨማሪ ግቦች ሳይስተናገዱበት በፈረሰኞቹ የ1ለ0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ12 ጊዜ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለ5 ጊዜ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በጨዋታው ባሳየው እንቅስቃሴ ሰልሀዲን በርጌቾ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል፡፡


ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ በ8 ሰአት ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ጅማ አባጅር በሁለተኛው አጋማሽ በ65ተኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ቆለቻ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሄኖክ አዱኛ በዘንድሮው ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል፡፡

ከሁለቱም ጨዋታዎች መጠናቀቅ በኃላ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ሽልማቶችን አበርክተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ቡናው ወንድይፍራው ጌታሁን በምድብ ጨዋታ ላይ አዲስአበባ ከተማ ላይ ከረጅም ርቀት ባስቆጠራት ግብ የውድድሩ ምርጥ ግብ አሸናፊ በመሆን የ5 ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ፣ የጅማ አባጅፉሩ ሳምሶን ቆለቻና የኢትዮጵያ ቡናው ሳሙኤል ሳኑሚ በእኩል ሶስት ግቦች የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር በመጋራት ለሁለቱም የ10 ሺህ ብር ሽልማት ፣ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ካርሎስ ቫዝ ፔንቶና ኮንትዲቫራዊው የመሀል ሜዳ ተጫዋች አብዱልከሪም ኒኪማ ኮከብ አሰልጣኝና ተጫዋች በመባል የ20ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል፡፡




Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *