አስቻለው ታመነ ግምቱ ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ሙሉ የስፖርት ትጥቅ እና የልምምድ ቁሳቁሶች ለዲላ ከነማ የወንዶች እና ሴቶች ቡድን በስጦታ አበርክቷል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እና በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው አስቻለው ታመነ ትላንት ማምሻውን የዲላ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የሁለቱም ክለቦች (ዲላከተማ እና ጌዲዮ ዲላ) ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ግምቱ ከ100 ሺህ ብር በላይ የሆነ ከውጭ የመጡ የስፖርት መሳርያዎች እና የጨዋታ ማልያዎች በስጦታ መልክ አበረክቷል።
ከርክክቡ በኋላ አስቻለው ታመነ ባደረገው ንግግር ድጋፉን ለማድረገ ያነሳሳውን ምክንያ አብራርቷል፡፡ “ለሁን ለደረስኩበት የእግር ኳስ ህይወት ስኬት ሚስጢር ከልጅነት የፕሮጀክት ቡድን አንስቶ እየተጫወትኩበት ያደግኩበት ዲላ ከተማን መደገፍ ግዴታዬ ነው፡፡ በቀጣይ ቡድኑ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ በመሆን ትልቅ ደረጃ ደርሶ ማየትም እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ስጦታ የመጀመርያዬ ቢሆንም በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የዲላ ከተማ ም/ከንቲባ እንደተናገሩት አስቻለው ታመነ ትውልድ ከተማውን ያሳደገውን ክለብ አስታውሶ ይህን ትጥቅ በማበርከቱ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ድጋፎች ክለቡን ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ለሚያደርገው ጥረት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆነው ገልፀዋል።
በሃገሪቱ በትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ለትውልድ ከተማቸው የሚያደርጉት ድጋፍ አሁን አሁን እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ጌታነህ ከበደ (ዲላ)፣ ሽመልስ በቀለ (ሀዋሳ)፣ ሚካኤል ጆርጅ (ደሴ) አብዱልከሪም መሐመድ (ወንዶ ገነት) እና ኡመድ ኡኩሪ (ጋምቤላ) በተለያዩ ጊዜያት የትጥቅ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡