​የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ ለጥቅምት 19 ተራዝሟል

የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ ቀደም ብሎ ጥቅምት 11 ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወደ ጥቅምት 19 ለውጥ ተደርጎበታል፡፡
በክልሉ በሚገኙ 10 ክለቦች መካከል ጥቅምት 11 በሆሳዕና ከተማ ይደረጋል ተብሎ መርሀ ግብር የወጣለት የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ ከጥቅምት 19-27 በሆሳዕና ከተማ ይካሄዳል፡፡ የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን በሚሰጠው የስፖርታዊ ጨዋነት ስልጠና እና በሌሎች በርካታ ስራዎች ምክንያት ውድድሩ እንደተራዘመ የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጥቅምት 25 እና 26 በሚደረጉ ጨዋታዎች እንደሚጀምር ፌዴሬሽኑ ማሳወቁን ተከትሎ የካስቴል ዋንጫው መርሀ ግብር ይጋጫል ቢባልም የክልሉ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የከፍተኛ ሊግ ውድድር እንዲራዘምላቸው በጠየቁት መሰረት ቀኑ ባይታወቅም ለማራዘም እንደወሰነ የጽህፈት ቤት ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *