​የእለቱ ዜናዎች፡ ጥቅምት 17 ቀን 2010

በኢትዮጵያ እግርኳሰ ዛሬ የተሰሙ መረጃዎችን እንዲህ ባለ መልኩ አቅርበንላችኋል፡፡

ወንድምኩን አላዩ

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን አስቀድሞ በህዝብ ግኑኝነት በኋላም ያለፈውን አንድ አመት በፌዴሬሽኑ ዋና ፀኃፊነት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ወንድምኩን አላዩ ከፍተኛ የሆነ ህመም ያጋጠማቸው መሆኑ የታወቀ ሲሆን የህመማቸው ምክንያት ከፍተኛ ሆነ የስራ ጫና እንደሆነ ተገልጿል። አቶ ወንድምኩን አሁን ህክምናቸውን እየተከታተሉ ሲሆን ምን አልባትም ከጤናቸው አሳሳቢነት እና ካለባቸው የስራ ጫና አንፃር ከፌዴሬሽኑ ኃላፊነት እራሳቸውን ሊያገሉ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።

ደደቢት

የደደቢት የሴቶች ቡድንን ዋና አሰልጣኝነት በመያዝ ክለቡን የ2009 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ያደረጉት ጌቱ ተሾመ የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ረዳት ሊሆኑ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል። በምትካቸውም የታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሴቶች ቡድኑን እንደሚረከቡ ተገምቷል። አሰልጣኝ ጌቱ በተጨዋችነት ዘመናቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ በኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ፣ በመድን እንዲሁም በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን አሳልፈዋል፡፡

የፎቶ አውደርዕይ

በጋዜጠኛ ታሪኬ ቀጭኔ የተዘጋጀው የቀደምት ስፖርተኞች አውደርዕይ በቂርቆስ ቤተክርስቲያን አጥር ላይ በተዘጋጁ ምስሎች እየተደረገ ይገኛል፡፡ አላማው ከቂርቆስ እና አካባቢው ወጥተው በኢትዮጵያ ስፖርት ጉልህ ተፅዕኖ የፈጠሩ ስፖርተኞችን ለማሰብ እንደሆነ የአውደ ርዕዩ አዘጋጅ ጋዜገኛ ታሪኬ ቀጭኔ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡ ፎቶዎቹ እስከ እሁድ ድረስ ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን የስፖርት አፍቃርያንም በስፍራው ተገኝተው እንዲጎበኙ ተጋብዟል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔ

የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ሊካሄድ የቀናት እድሜዎች በቀሩት በአሁኑ ወቅት አስቀድሞ አፋር ሰመራ ይካሔዳል ቢባልም ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ወደ አዲስ አበባ መቀየሩ የሚታወስ ነው። ከጠቅላላው ጉባኤ በፊት አስገራሚ ነገሮች እየተሰሙ ሲሆን አሁን ደግሞ ውድድሮችን በተለያዩ ምክንያቶች በማራዘም የሚታወቀው ፌዴሬሽኑ ጥቅምት 30 ይካሔዳል ተብሎ ቀን የተቆረጠለት ጠቅላላ ጉባኤን ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወደ ሌላ ቀን ሊለወጥ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮዽያ ቡና ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒችን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ለመቅጠር ከስምምነት መድረሱ የተሰማ ሲሆን በቅርቡ አሰልጣኙ ወደ ኢትዮዽያ በመምጣት ክለቡን በይፋ እንደሚቀላቀሉ ተነግሯል። የ57 አመቱ አሰልጣኝ ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ እና በታንዛንያ ክለቦች ሰርተዋል፡፡

አብዱልከሪም ሀሰን ከኢትዮዽያ ቡና ጋር በስምምነት መለያየቱ ዛሬ በወሰደው የመልቀቂያ ደብዳቤ ተረጋግጧል፡፡ አብዱልከሪም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለቆ ለኢትዮዽያ ቡናን ባለፈው አመት ቢቀላቀልም ብዙም የመሰለፍ እድል ካለማግኘት ጋር በተያያዘ ምክንያት ከክለቡ ጋር መለያየቱ ታውቋል፡፡ አብዱልከሪም ሀሰን ከሦስት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ተያይዞ ስሙ እየተነሳ ሲሆን በቅርብ ቀናት ቀጣይ ማረፊያው ይለያል ተብሏል፡፡

አቃቤ ህግ

በ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታ ተከስቷል በተባለው የጨዋታ ውጤት አላግባብ የማስቀየር ሙከራ ዙርያ ለወራት የዘለቀው ምርመራ መቋጫ ሊያገኝ ይመስላል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እስካሁን የቀረቡት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ጉዳዩን ለማብራራት የሚበቃ እንዲሁም ተፈፀመ ስለተባለው ጉዳይ ፍንጭ የሚሰጥ ባለመሆኑ ክስ ለመመስረት የማያስችል መሆኑን አስታውቋል፡፡ የአቃቤ ህጉ ምላሽ መታወቁን ተከትሎ በፌዴሬሽኑ በኩል ያለው ውሳኔ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

መቐለ ከተማ

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፈው መቐለ ከነማ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ከአሰልጣኝነት አሰናብቶ የቀድሞው የደደቢት እና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ከቀጠረ በኋላ የተለያዩ ለውጦችና ተጨማሪ ተጨዋቾችን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ትላንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ጥቅምት 25 አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማን ከመግጠሙ በፊት ከመከላከያ (ነገ 03:00 ጎፋ ሜዳ)፣ ደደቢት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡  አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወደ አአ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት መቐለ ከተማ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

_________________________

ነገ በሶከር ኢትዮጵያ

የቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ (አል አህሊ ከ ዋይዳድ ካዛብላንካ)

የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ቅድመ ዳሰሳ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ)

_________________________

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *