[በለጠ ኢርቤሎ ከሆሳዕና]
የደቡብ ክልል የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን የሚያሳትፈው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ዛሬ እሁድ ጥቅምት 19 በሆሳዕና ተጀምሯል፡፡ አስቀድሞ እንደተገለፀው በውድድሩ 10 ክለቦች ይሳተፋሉ ተብሎ የተገለፀ ቢሆንም ዛሬ ጠዋት በነበረው የእጣ አወጣጥ ሥነ-ስረዓት የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ወልቂጤ ከተማ እና ዘንድሮ ከፍተኛ ሊጉን የተቀላቀለው ቡታጅራ ከተማ እንደማይሳተፉ ተረጋግጧል፡፡ ከፋ ቡና ደግሞ የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ረፋድ ላይ በወጣው የእጣ ማውጣት ስነስርዓት ክለቦቹ በዚህ መልኩ ተደልድለዋል፡፡
ምድብ ሀ
ሀዲያ ሆሳዕና፣ ዲላ ከተማ፣ ስልጤ ወራቤ፣ ሀላባ ከተማ
ምድብ ለ
ሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ቤንች ማጂ ቡና፣ ደቡብ ፖሊስ
08:00 ላይ በመክፈቻው አዘጋጁ ሀዲያ ሆሳዕና ከዲላ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ግብ በማስቆጠር ሀዲያ ሆሳዕናዎች በኢብሳ በፍቃዱ ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ዲላ ከተማዎች ተከተል ታደለ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል፡፡ በጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕና ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም ወደ ጎል መቀየር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ብዙም ማራኪ ያልነበረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል::
10:00 ላይ በምድብ ሀ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ አራት ግቦች ተቆጥረው ሀላባ ከተማ እና ስልጤ ወራቤ 2-2 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ሁለቱም ክለቦች በጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ከማድረጋቸውም ባሻገር ሙሉ 90 ደቂቃ እጅግ ማራኪ እና የተመልካችን ቀልብ የሳበም ጨዋታ ተደርጓል፡፡
ስልጤ ወራቤ ከድር ታረቀኝ ቀዳሚ ሲሆን ሀላባ ከተማ ተመስገን ይልማ በተከታታይ ባስቆጠራቸው ጎሎች መሪ በመሆን የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ ከእረፍት መልስ ተጭኖ መጫወት የቻለው ስልጤ ወራቤ ኢስማኤል ሬድዋን የአቻነቷን ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤተ ተጠናቋል፡፡
የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ውድድር እስከ ጥቅምት 26 የሚቀጥል ሲሆን ዛሬ በነበረው የመክፈቻ ጨዋታ በርካታ ተመልካች በአቢዮ ኤርሳሞ በመገኘት ጨዋታዎችን ሊታደም ችሏል፡፡ የምድብ ለ ጨዋታም በነገው እለት የሚከናወን ይሆናል፡፡