ለአንድ ሳምንት በሰበታ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የኦሮሚያ ዋንጫ በባለሜዳው ክለብ ሰበታ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በቅድሚያ 07:20 ላይ በተደረገው የደረጃ ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲ በመለያ ምቶች አሸንፎ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ ጨዋታው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግብ ያልተስታገደ ሲሆን ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራም እምብዛም ሳይስተናገድበት ቀርቷል፡፡ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች ለገጣፎ ለገዳዲ 4-3 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
9፡30 የጀመረው የሰበታ ከተማ እና የጅማ አባቡና ጨዋታ በዛ ያለ የስፖርት ቤተሰብ የታደመበት ነበር፡፡ በፈጣን እንቅስቃሴ የበተጀመረው ጨዋታ ሰታ ከተማ ጎል ለማስቆጠር የፈጀበት9 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ኤፍሬም ቀሬ ያሻገረውን ኳስ ዓብይ ቡልቲ በአግባቡ ተጠቅሞ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ቡናዎች በቴዎድሮስ ታደሰ እና ሐይደር ሸረፋ አማካይነት አቻ ለመሆን የግብ እድል ቢፈጥሩም የአባ ቡና የተከላካይ መስመርን ሲረብሸ የዋለው አብይ ቡልቲ በ35ኛው በድጋሚ አስቆጥሮ የሰበታን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡
ከዕረፍት መልስ በ48ኛው ደቂቃ ኳስ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ኤፍሬም ቀሬ ወደ ግብነት ለውጦ የባለሜዳዎቹን መሪነት ወደ ሶስት ሲያሰፋ በ75ኛው ደቂቃ ሐይደር ሸረፋ በግምት ከ30 ሜትር አክርሮ በመምታት ጅማ አባ ቡናን ከሽንፈት ያላዳነች ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሰበታ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሽልማት ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ላይ ለተሳተፉ እና አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለአሸናፊው ሰበታ ከተማ ዋንጫ ተበርክቷል፡፡