የኢትዮጵያ ዜናዎች – በዳንኤል መስፍን
ቻን
የኢትዮዽያ የቻን ተሳትፎ አሁንም ቁርጡ አለየለትም፡፡ ፌዴሬሽኑም እስካሁን በጉዳዩ ዙርያ ያለው ነገር የለም፡፡ ካፍ ጥቅምት 26 አአ ላይ የመጀመርያውን ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር እንዲጫወት መርሀ ግብር ማውጣቱን ተከትሎ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሪምየር ሊጉ ውድድር በተባለበት ቀን እንዲጀመር በማሰብ ለካፍ ከሩዋንዳ ጋር የሚኖረው ጨዋታ ህዳር 3 እና 10 እንዲሆኑ በመጠየቅ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል። ጉዳዮን የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ እየተመለከቱት እንደሆነ የተሰማ ሲሆን ምላሹ መልካም ሆኖ የቀን ለውጡ ተቀባይነት ካገኘ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የሚጫወት ይሆናል። ሆኖም ካፍ አላራዝምም ካለ ኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የማይሳተፍ ይሆናል ተብሏል።
ውሳኔ
የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፒሊን ኮሚቴ በሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ጨዋታ ላይ ሊፈፀም ያለ የጨዋታ ማጭበርበር ሙከራ ነበር በሚል ሲከታተለው የቆየውን ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ ጉዳዩን መመልከት የጀመረ ሲሆን በእነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የፌዴራል አቃቤ ህግ ሦስቱ ተጨዋቾች ሊያስከስሳቸው የሚችል አሳማኝ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ አላገኘሁም በማለት ተጨዋቾቹን ነፃ ናቸው ብሎ መሸኘቱ ይታወሳል።
ኤፍሬም ዘካርያስ
የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች ኤፍሬም ዘካርያስ ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ፊርማውን ለማኖር ዛሬ በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቢገኝም “የአንተ ጉዳይ ውሳኔ ያላገኘ በመሆኑ ጥያቄህን ለማስተናገድ እንቸገራለን” በማለት ፌዴሬሽኑ እንደመለሰው ታውቋል፡፡ በተጫዋቹ ጉዳይ ላይ በዚህ ሰሞን የመጨረሻ ውሳኔ የሚጠበቅ ሲሆን ውሳኔው ተጨዋቹን ነፃ የሚያወጣው ከሆነ ለቀጣይ የውድድር አመት ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።
ፕሪምየር ሊግ
የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በተያዘለት ጥቅምት 25 እንደሚጀምር ታውቋል። የውድድር ስነ ስርአት እና ማዘውተርያ ስፍራዎች ዳሬክተር አቶ ሰለሞን ለሶከር ኢትዮዽያ እንደተናገሩት ከሆነ ውድድሩ አስቀድሞ በወጣለት መርሀግብር እንደሚከናወንና ተሳታፊ ክለቦችም እንዲዘጋጁበት መመርያ መተላለፉን ገልፀው ውድድሩ የሚራዘምምበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አሳውቀዋል።
ከ17 አመት በታች ሴቶች
የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ነገ ዝግጅቱን በድጋሚ ሊጀምር ነው። በፈረሳይ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም ከ17 አመት በታች ዋንጫ መጀመርያውን የማጣርያ ጨዋታ ኬንያ አልሳተፍም ማለቷን ተከትሎ ዝግጅቷን ያቋረጠችው ኢትዮጵያ ነገ በድጋሚ አዳዲስ ተጨዋቾች በማካተት ዝግጅቷን ለተወሰኑ ቀናት እንደምታደርግ ሰምተናል። የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች የሴቶች ቡድን በቀጣይ ህዳር ወር ከናይጄርያ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
ምርመራ
የኢትዮዽያ ከ17 እና 20 አመት በታች የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች የMRI ምርመራ ተጀምሯል፡፡ ከወዲሁ ክለቦች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች ምርመራውን እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ከህክምናው ቡድኑ እናደገኘነው መረጃ ከሆነ እስካሁን ወደ ከ400 በላይ ታዳጊዎች ምርመራ ያደረጉ ሲሆን እስካሁን የአላፊዎቹ በቁጥር ባይታወቁም ከአምናው በተሻለ ሁኔታ ክለቦች ተገቢ የሆኑ ተጨዋቾችን ይዘው በመምጣት ምርመራ እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል። ያም ቢሆን ክለቦች አሁንም ዕድሜያቸው ያለፉ ታዳጊዎችን ይዘው ቢመጡም ምርመራ እየጣላቸው ሊወድቁ ችለዋል ተብሏል። የኢትዮዽያ ከ17 እና 20 አመት በታች የፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን የህክምናው ምርመራ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚሆን ሰምተናል።
ኦሮሚያ ዋንጫ (ባቱ)
በባቱ ከተማ አስተናጋጅነት በ6 የከፍተኛ ሊግ እና 1ኛሊግ ቡድኖች መካከል ከጥቅምት 14 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኦሮሚያ ዋንጫ ነገ ፍፃሜውን ያገኛል። በዙር ውድድር ባስመዘግቡት የነጥብ ብዛት አሸናፊው በሚለይበት በዚህ ውድድር ነገ 04:00 ላይ ቡራዩ ከተማ ከ መቂ ከተማ፣ በ07:00 ሞጆ ከተማ ከ ቡልቡላ፣ በ09:00 አርሲ ነገሌ ከ ባቱ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል። ምድቡን በቡራዩ ከተማ በ10 ነጥብ (+5) ሲመራ አርሲ ነገሌ በ10 ነጥብ (+1) ሁለተኛ እና መቂ ከተማ 7 ነጥብ (+1) በመያዝ 3ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በ12 ቡድኖች መካከል ከህዳር 8 ጀምሮ በዱከም ከተማ የኦሮምያ ዋንጫ በብሔራዊ ሊግ ቡድኖች መካከል እንደሚካሄድ ሰምተናል።
የአፍሪካ ዜናዎች – ኦምና ታደለ
ዩጋንዳ
ዩጋንዳ አዲስ አሰልጣኝ ፍለጋዋን አሁንም ቀጥላለች፡፡ እንደቢቢሲ ስፖርት ዘገባ ከሆነ ከ100 በላይ አሰልጣኞች ለክሬንሶቹ ስራ ፍላጎታቸውን ያሳዩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የቶጎ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ክላውድ ለርዋ ይገኙበታል፡፡ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ከዩጋንዳ ጋር ተለያየተው ወደ ደቡብ አፍሪካ ካቀኑ ወዲህ ያለፉት ሁለት ወራት ምክትል አሰልጣኙ ሞሰስ ባሴና በግዜያዊነት እየመሩት ይገኛሉ፡፡ ባሴና እንደለርዋ ሁሉ ብሄራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን ፍላጎት ያሳዩ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ዩጋንዳ በቅርብ ዓመታት በገነባቸው ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ምክንያት በአሰልጣኝነት ለመስራትም የሚፈልጉ ባለሙያዎች ብዛትም አሻቅቧል፡፡
ግብፅ
የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ የሆነው አል አህሊ ወደ ካዛብላንካ ከማቅናቱ በፊት ዛሬ የመጨረሻውን ልምምድ ሲሰራ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች መታደማቸው አስገራሚ ሆኗል፡፡ አህሊ በሜዳው ደጋፊዊ ፊት በመጀመሪያው ጨዋታ ከዋይዳድ ካዛብላንካ ጋር አቻ የተለያየ ሲሆን ቅዳሜ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ዝግጅት በርካታ ደጋፊዎች በልምምድ ስፍራው ተገኝተዋል፡፡ ይህንን ተክትሎም አህሊ በሺዎች ወደ ልምምድ ስፍራው በመትመማቸው ምክንያት አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ለመውሰድ ልምምዱን ሰርዞታል፡፡ የስምንት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አህሊ በአረቡ አለም በርካታ ሚሊየን ተከታዮች ያሉት ክለብ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ደጋፊዎች በብዛት ከወሳኝ ጨዋታዎች በፊት ወደ ልምምድ ሜዳ በርከት ብለው በመሄድ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ይስተዋላል፡፡