[ሪፖርት | በለጠ ኢርቤሎ – ከሆሳዕና]
ለ2ኛ ጊዜ በሆሳዕና ከተማ እየተደረገ ያለው የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ በሶስተኛ ቀን ውሎ ሀላባ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ድል ሲቀናቸው ቤንችማጂ ቡና እና ሀምበሪቾ ዱራሜ አቻ ተለያይተዋል፡፡
6:00 ሰዓት ላይ የጀመረው የሀላባ ከተማ እና የዲላ ከተማ ጨዋታ በሀላባ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሀላባ ከተማ በተመስገን ይልማ ግብ ቀዳሚ ቢሆኑም ሀብታሙ ፍቃዱ ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ዲላን አቻ አድርጓል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ስንታየሁ አሸብር ለሀላባ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሮ ሀላባን ወደ ድል መርቷል፡፡
8:00 ላይ ቀዝቀዝ ባለ ድባብ የተጀመረው የምድብ ለ የሀምበሪቾ ዱራሜ እና የቤንች ማጂ ቡና ጨዋታ ጎል ሳይቀጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
10:00 ሰዓት ላይ የጀመረው የእለቱ 3ኛ ጨዋታ በደጋፊ ድባብ ታጅቦ ሀዲያ ሆሳዕና ስልጤ ወራቤን 3-1 አሸንፏል፡፡ ሆሳዕና በመልካሙ ፉንዱሬ ግብ የመጀመሪያው ግማሽ በመሪነት ሲያጠናቅቅ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጭነው በመጫወት በዋቴሮ ኤልያስ እና መሐመድ ከድር አማካኝነት ተከታትለው በተቆጠሩ ግቦች መሪነታቸውን ወደ ሶስት አሳድገዋል፡፡ ስልጤ ወራቤ ከመሸነፍ ያላዳናቸውን ጎል ካሳ ከተማ በ71ኛው ደቂቃ በግሩም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው መገባደጃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናው ተከላካይ በረከት ወልደዮሐንስ እና የስልጤ ወራቤው ተከላካይ አካሉ አበራ በፈጠሩት ጠብ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ተወግደዋል፡፡
የደቡብ ካስቴል ዋንጫ በነገው እለት ጥቅምት 22 ቀን 2010 በሦስት ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡
ምድብ ለ
6:00 ደቡብ ፖሊስ ከ ቤንች ማጂ ቡና
ምድብ ሀ
8:00 ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀላባ ከተማ
10:00 ዲላ ከተማ ከ ስልጤ ወራቤ
ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ዜና ወልቂጤ፣ ቡታጅራ እና ካፋ ቡና በውድድሩ ላይ ያልተካፈሉበት ምክንያት ታውቋል፡፡ ወልቂጤ ከተማ በፋይናንስ እና በርካታ ተጫዋቾች በመጎዳታቸው እንዳልተሳተፈ ሲገለጽ ካፋ ቡና ውድድሩ የተካሄደበት ሆሳዕና ርቀት ከበጀት ጋር አለመጣጣሙ ተገልጿል፡፡ ቡታጅራ ከተማም የዝግጅት ጊዜ ማነስ እና የፋይናንስ እጥረት ላለመሳተፋቸው እንደምክንያት አቅርበዋል፡፡