የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ከሩዋንዳ ጋር ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ የመጀመርያውን ልምምድ በአዲስ አበባ ስታድየም አድርጓል።
ለካፍ ያቀረበው የጨዋታው እለት ይራዘምልኝ ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ጨዋታውን የማድረግ ግዴታ ውስጥ የገባው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን እሁድ ከሩዋንዳ ጋር ላለበት የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ ከ09:00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመርያ ልምምዱን አድርጓል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከጠሯቸው የ27 ተጨዋቾች መካከል ሳላዲን ሰዒድ፣ ጋዲሳ መብራቴ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ዳዋ ሁቴሳ ያልተገኙ ሲሆን ለመጀመርያ ጊዜ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበላቸው ኄኖክ አዱኛ ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና እሸቱ መናን ጨምሮ 23 ተጫዋቾች በዛሬው ልምምድ ላይ ተሳትፈዋል። በልምምድ ወቅት ደግሞ ቴዎድሮስ በቀለ እጁ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ልምምዱን አቋርጦ ወጥቷል።
በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ለጨዋታ በበቂ ሁኔታ ለማዘጋጀት ይረዳ ዘንድ በእሁዱ ጨዋታ ላይ ቋሚ ተሰላፊ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጨዋቾችን ለሁለት ከፍለው እንዲጫወቱ በማድረግ የማቀናጀት ስራ ሲሰሩ ተመልክተናል።
ከልምምድ በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ስለ ዝግጅታቸው እና ተጠርተው ስላልመጡት ተጫዋቶች ተናግረዋል፡፡ “ሳላዲን ሰዒድ እና ጋዲሳ መብራቴ ክለቡ ጉዳት ላይ ናቸው በማለቱ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ ዳዋ ሆቴሳ እና ሱራፌል ዳኛቸው ደግሞ ጥሪ ከመጥራታችን በፊት ወደ ወልድያ በማቅናታቸው እስኪመለሱ ያለው የቦታው ርቀት አስቸጋሪ በመሆኑ ከቡድኑ የማይቀላቀሉ ሆኗል፡፡ እንግዲህ ዛሬ ዝግጅታችንን ጀምረናል በዛሬው ልምምድ ባየነው ነገር ደስተኛ ነን፡፡ እንደተመለከታችሁት የማቀናጀት ፣ የታክቲካል ዲሲፒሊን ስራ ሰርተናል፡፡ ሳላዲን ቢኖር ኖሮ ለቡድናችን ማጥቃት ትልቅ ጉልበት ይሆነን ነበር። ዞሮ ዞሮ ባሉን ልጆች የተሻለ ነገር ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው። እሁድ ወደ ሜዳ የምንገባው ለማሸነፍ ነው የሚሆነውን አብረን እናየዋለን” ብለዋል።
የኢትዮዽያ እና ሩዋንዳ ጨዋታ የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም 10:00 ላይ ይደረጋል፡፡