የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጀርመናዊው አሰልጣኝ አንቶኒ ሄይ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የሚያመሩትን 18 ተጫዋቾች ይፋ አድርገዋል፡፡ በመጪው እሁድ ለሚደረገው ጨዋታ አማቩቢዎቹ አርብ 10፡00 ወደ አዲስ አበባ የሚበሩ ይሆናል፡፡
አሰልጣኝ ሄይ ከዚህ በፊት በነበሩት የማጣሪያ ጨዋታዎች ያልተሳተፉ 8 ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ሲቀላቅሉ ግብ ጠባቂው ኤሪክ ንዳይሽምዬ እና አማካዩ ጂሃድ ቢዚማና አሁንም በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል፡፡ የራዮን ስፖርትሱ የመሃል ተከላካይ ሳዳም ኒዋንድዊ ለመጀመሪያ ግዜ ለሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን የተጠራ ተጫዋች ሁኗል፡፡ ቢዚማና እረቡ እለት ባጋጠመው መጠነኛ ጉዳት ከልምምድ አቋርጦ ቢወጣም ዛሬ በአማሆሮ ስታዲየም በተደረገው የመጨረሻ ልምምድ ላይ ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሷል፡፡ “የቡድኑ ምክትል አምበል ጂሃድ ቢዚማና ባጋጠመው ጉዳት ለጨዋታው አይደርስም ቢባልም አሁን በመልካም ጤንነት ላይ በመገኘቱ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ ተካቶ ወደ አዲስ አበባ ይጓዛል::” ሲል ሩዋንዳዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ጃን ሉክ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡ ስምንት ተጫዋቾች ከሃያሉ ራዮን ስፖርትስ ሲመረጡ ከተቀናቃኙ ኤፒአር ሶስት ተጫዋቾች ተካተዋል፡፡ ቡድኑ ከሰኞ ጀምሮ ጠንካራ ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
አሰልጣን ሄይ ዛሬ የመጨረሻ ስብስባቸውን ይፋ ሲያደርጉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አስፈላጊውን መረጃ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ “በተጋጣሚያችን ኢትዮጵያ ላይ ጥናት አካሂደናል፡፡ የስራ ባልደረባዬ የሆነውን የሱዳን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ (መሃመድ ማዝዳ) ኢትዮጵያን አሸንፎ ወደ ቻን በማምራቱ አናግሬው ነበር፡፡ በጣም እርግጠኛ ነኝ ሁሉንም ነገር በጥሩ መልኩ ከተጓዘ የተሻልን ቡድን ስለሆንን ለቻን እናልፋለን፡፡ ግን በእግርኳስ የሚፈጠረው አይታወቅም ስለዚህም ሁሉም ነገር ክፍት ነው፤ ይህ ደግሞ ስፖርቱን ሳቢ የሚያደርገው ነገር ነው፡፡ ቢሆንም እንዳቀድነው ሁሉም ነገር ከሄደ እናልፋለን ምክንያቱም እኛ የተሻለው ቡድን፣ በፊፋ ደረጃም በጣም የተሻልን እና በተጫዋቾቻችንም የግል ብቃት ብልጫ ስላለን ነው፡፡” ሲሉ ሄይ በቡድናቸው ላይ ያላቸውን ከፍተኛ የራስ መተማመን ጠቁመዋል፡፡
የቡድኑ አምበል ንዳይሽምዬ በበኩሉ “ለፈታኙ የኢትዮጵያ ጨዋታ ሁላችንም ተዘጋጅተናል፡፡ በነሃሴ ወር በዩጋንዳ ተሸንፈን ያጣነውን የማለፍ ተስፋ አሁን ላይ ዳግም በሌላ ጨዋታ የማለፍ እድል አግኝተናል፡፡ ለስህተት ቦታ የለንም፡፡ በአእምሮ፣ በአካላዊ እና ስነ-ልቦና ደረጃ ሩዋንዳን ወደ ቻምፒየንሺፑ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል፡፡” ሲል ለሩዋንዳው RUHAGOYACH.com አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ጨዋታ እሁድ 10፡00 የሚደረግ ሲሆን አማቩቢዎቹ አርብ ከሰዓት ኪጋሊን ለቀው ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመሩ የሩዋንዳ እግርኳስ ፌድሬሽን አስታውቋል፡፡ ፌድሬሽኑ ጨምሮ በቻን ማጣሪያው ምክንያት የአዛም ሩዋንዳ ፕሪምየር ሊግ 5ተኛ እና 6ተኛ ሳምንት የጨዋታ ቀኖች ላይ መሸጋሸግ ማድረጉም አሳውቋል፡፡
ሙሉ የቡድኑ ስብስብ ይህንን ይመስላል
ግብ ጠባቂዎች
ኤሪክ ንዳይሽምዬ (ራዮን ስፖርትስ)፣ ማርሴል ንዛሮራ (ፖሊስ)
ተከላካዮች
ፋውስቲን ኡሲንጊማና፣ ኤሪክ ሩታንጋ፣ ሳዳም ኒዋንድዊ፣ ቴሪ ማንዚ (ሁሉም ከራዮን ስፖርትስ)፣ ኤሪክ ኢራዱኩንዳ፣ ሶተር ካዩምባ (ሁለቱም ከኤኤስ ኪጋሊ)፣ ክሌስተን ንዳይሽምዬ (ፖሊስ)
አማካዮች
ጂሃድ ቢዚማና፣ ሙሃጂር ሃኪዚማና ( ሁለቱም ከኤፒአር)፣ ኦሊቨር ኒዮንዚማ፣ ያኒክ ሙኩንዚ (ሁለቱም ከራዮን ስፖርትስ)፣ አሊ ንዮንዚማ (ኤኤስ ኪጋሊ)
አጥቂዎች
ኢነሰንት ንሹቲ (ኤፒአር)፣ ጀስቲን ሚኮ፣ አቢዲ ቢራማሂር (ሁለቱም ከፖሊስ)፣ ጃቤል ማኒሺምዌ (ራዮን ስፖርትስ)