የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በክልል ከተሞች መደረግ ሲጀምሩ ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር ሀዋሳ ከተማን ያስተናድጋል። ከቀኑ 9፡00 ላይ በሚጀምረው በዚሁ ጨዋታ ዙሪያ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አሰናድተናቸዋል።
በ2009 የከፍተኛ ሊጉ ቻምፒዮን በመሆን ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀለው ጅማ አባ ጅፋር ቡድኑ ላይ በርካታ ለውጦችን በማድረግ ለአዲሱ የውድድር አመት ራሱን ሲያዘጋጅ ከርሟል ። አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በክረምቱ አጋማሽ በአሰልጣኝነት የሾመው አባጅፋር የቡድን ስብስባቸውን በአዲስ መልክ ካወቀሩ የሊጉ ክለቦች መሀከል አንዱ ነው። 11 አዳዲስ ተጨዋቾች ከፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ክለቦች ያስፈረመ ሲሆን አራት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾችም ክለቡን ተቀላቅለዋል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ዘጠኝ ተጨዋቾችን የለቀቀው ሀዋሳ ከተማ በምትካቸው ሰባት የሀገር ውስጥ ተጨዋቾችን አስፈሟል። በተለይ ሁለት አመታትን ከተጨዋችነት ርቆ የነበረው አንጋፋው አማካይ ሙሉአለም ረጋሳን ከቡድኑ ጋር መቀላቀሉ በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ማለፉ የሚታወስ ነው። ከእንዚህ ዝውውሮች ባሻገርም ሀዋሳ ከተማ በቅርቡ አንድ ጋናዊ ተከላካይ ከማስፈረሙ ሌላ አምስት የሚሆኑ ተጨዋቾችንም ከ20 ዐመት በታቹ ቡድኑ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል ።
ሁለቱ ቡድኖች በነበራቸው የዝግጅት ጊዜ የተሳተፉባቸውን ውድድሮች ስንመለከት ጅማ አባ ጅፋር በተጋባዥነት በተወዳደረበት የአዲስ አበባ ዋንጫ ጥሩ ፉክክር በማድረግ በሶስተኝነት ሲያጠናቅቅ ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በሽንፈት በጀመረበት የደቡብ ካስትል ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።
ጅማ አባጅፋር በርካታ አዲስ ፈራሚዎቹን በተጠቀመበት የአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ከወገብ በታች ያለው የቡድኑ ክፍል በጥንካሬ የሚነሳ ነበር። አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ አምና በሊጉ ሁለተኛ ዙር በጅማ አባ ቡና ከነበራቸው ቡድን ጋር በሚመሳሰል መልኩ በአባ ጅፋርም በቀላሉ ጎል የማያስተናግድ እና በራሱ የሜዳ ክፍል ለተጋጣሚዎቹ ክፍተት የማይሰጥ አይነት ቡድን ገንብተዋል። ጨዋታው እንዲህ አይነት ጠንካራ ጎን ያለውን ቡድን አጥቅቶ በመጫወት እና ግቦችን በማስቆጠሩ ረገድ የተሻለ የሚባል አቅም ካለው ሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያገናኝ መሆኑ ይበልጥ ተጠባቂ ያደርገዋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር በበርካታ የኳስ ንክኪዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የሚታወቀው ሀዋሳ ከተማ በቀላሉ ከማይታለፈው የአባ ቡና የአማካይ እና የተከላካይ ክፍል ጋር የሚኖረው ፍልሚያ የጨዋታውን ውጤት ሊወስኑ ከሚችሉ ነጥቦች መሀል ሊጠቀስ የሚገባው ነው። በአመዛኙ በመስመር አማካዮቹ ላይ የተንተራሰው የአባ ጅፋር የማጥቃት አጨዋወት በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጥያቄ ቢነሳበትም ቡድኑ ጨዋታውን ሜዳው ላይ እንደማድረጉ መጠን የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል። በዚህም አምና በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ የታየውና በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ ግን በሶስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስተናገደው የሀዋሳ የተከላካይ መስመር ሊፈተን ይችላል። በተለይ የቡድኑ የግራ መስመር ተከላካይ ደስታ ዮሀንስ አለመኖሩን ተከትሎ ለአባ ጅፋር ጠንካራ የቀኝ መስመር ጥቃት የሚሰጠው ምላሽ ተጠባቂ ይሆናል።
ዳንኤል ደርቤ በጉዳት ምክንያት እንዲሁም ደስታ ዮሀንስ እና ፍሬው ሰለሞን ለብሔራዊ ቡድን የተደረገላቸውን ጥሪ ተከትሎ በነገው ጨዋታ ላይ ለሀዋሳ ከተማ አገልግሎት የማይሰጡ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በፌዴሬሽኑ የስድስት ወራት ዕገዳ የተጣለባቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድናቸውን መምራት ባለመቻላቸው ሀዋሳ ከተማ በረዳቱ ሙሉጌታ ምህረት አማካይነት ለጨዋታው እንደሚቀርብ ይጠበቃል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ደግሞ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኄኖክ አዱኛ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ ውስጥ በመከታቱ ከነገው የቡድኑ ስብስብ ውጪ ሆኗል።