በተስተካካይ ጨዋታ መከላከያ ደደቢትን አሸነፈ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መደበኛ መርሃ ግብር እሁድ እለት በይፋ ቢጠናቀቅም መከላከያ በናይል ቤዚን ቻምፒዮን ሺፕ ውድድር ምክንያት ባልተጫወታቸው ጨዋታዎች ምክንያት የሊጉ ሙሉ ለሙሉ የመጠናቀቂያ ጊዜ እስከ ረቡእ ተራዝሟል፡፡

10 ሰአት በተጀመረው ጨዋታ መከላከያ ደደቢትን 2-1 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ደደቢት ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ተጠባባቂ ቡድኑን ይዞ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ጨዋታው ለማሟያ ካልሆነ በቀር ብዙም ፋይዳ የሌለው ጨዋታ እንደመሆኑ በቀጣይ ሳምንት ለሚደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ ዋና ዋና ተጫዋቾችን አሳርፈው ተጫውተዋል፡፡

ለመከላከያ የድል ግቦቹን መዳህኔ ታደሰ በጨዋታ እና ፍሬው ሰለሞን በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጠሩ ጋናዊው ሳሙኤል ጋንሳ የደደቢትን ብቸኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ድሉን ተከትሎ መከላከያ በ42 ነጥቦች የዘንድሮውን ፕሪሚየር ሊግ በ3ኝነት ሲያጠናቅቅ የአምናው ቻምፒዮን ደደቢት ከአምናው እጅግ አሽቆልቁሎ የውድድር ዘመኑን በ9ኛነት አጠናቋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2006 አም. በኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) በድጋሚ ይፋለማሉ፡፡

ያጋሩ