የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሶስት ጨዋታዎች ሲጀመር በሜዳው መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታድየም አዳማ ከተማን ያስተናገደው ወልዲያ በአንዷለም ንጉሴ እና ኤዶም ኮድዞ ግቦች በመታገዝ 2-0 በማሸነፍ አመቱን በድል ከፍቷል፡፡
በደማቅ ህብረ ዝማሬ እና በዛ ባለ የደጋፊ ድባብ በሼህ መሀመድ አሊ አላሙዲ ስታድየም 9፡00 ላይ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በነሀሴ ወር ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት የቀድሞው የወልድያ ተጫዋች እና አሰልጣኝ አቶ መሐሪ አምዴ የህሊና ፀሎት ተድርጓል፡፡
የጨዋታው መጀመሪያዋቹ 15 ደቂቃዎች እምብዛም ጠንካራ ሙከራ ያልታየባቸው እና ኳስ ወደ ሁለቱም ቡድኖች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ያልደረሰችባቸው ሆነው አልፈዋል፡፡ የጨዋታው ቀልብ የሚስብ እንቅስቃሴ የታየውም በ17ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁቴሳ ጎል ባስቆጠረበት አጋጣሚ ቢሆንም ጎሉ ከጨዋታ ውጭ የነበረ በመሆኑ ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡ ይህ ነው የሚባል ጥሩ እንቅስቃሴ ሳይታይበት በተጠናቀቀው በዚሁ የመጀመሪያ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ወልዲያዎች ወደ ጎል መቅረብ የቻሉት በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር። አዲስ ፈራሚው ፍፁም ገ/ማርያም በ19ኛው እና በ38ኛው ደቂቃዎች ላይ ሙከራዎች ቢያደርግም ከመረብ ጋር መዋሀድ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ሙሉ ለሙሉ የተሻለ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት እና ግቦችንም የተመለከትንበት ነበር። በሙከራ ረገድም ተሻሽለው የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች በተደጋጋሚ ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይተዋል። በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት አዳማ ከተማዎች በአዲስ ህንፃ እና ከነዐን ማርክነህ አማካኝነት ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
ከአዳማ በተቃራኒው ሁኔታ ኳስ መስርተው በመጫወት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመግባት ይሞክሩ የነበሩት ወልዲያዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ የተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸው በግራ የሳጥኑ ክፍል ላይ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ፍፁም ገ/ማርያም ያሻገረውን ኳስ ለማስጣል ሲል ምኞት ደበበ በሰራው ጥፋት ምክንያት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አንጋፋው አጥቂ አንዷለም ንጉሴ ወደ ግብነት ቀይሯት ወልዲያን ቀዳሚ አድርጓል። አምና የወልዲያን የውድድር መዘን የመጀመርያ ጎል ማስቆጠር የቻለው አንዷለም ዘንድሮ ደግሞ በ2010 ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ጎል አስቆጣሪ መሆን ችሏል፡፡
ከጎሉ በኋላ አዳማዎች 87ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሚሆኑበትን ዕድል በዳዋ ሁቴሳ አማካይነት ቢፈጥሩም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ዳዋ ሶስት የወልድያ ተከላካዮችን በማለፍ የሞከረውን ይህን ኳስ የወልድያው ግብ ጠባቂ ኤሚክሪል ቤሊንጌ አድኖበታል።
ነጥብ ከመጋራት ለጥቂት የተረፉት ወልድያዎች ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ኤደም ሆሶውሮቪ ከብሩክ ቃልቦሬ የተላከለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር የወልድያን መሪነት አስተማማኝ ማድረግ ችሏል፡፡ ኤደም የመጀመርያው ግብ ማስቆጠር የቻለው አንዷለምን ተክቶ በሜዳ ላይ ለ6 ደቂቃዎች ብቻ ቆይቶ ነው ጎል ማስቆጠር የቻለው፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልድያ
” ቡድናችን በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበረም። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ በተቻለን መጠን ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። ይህም በመሆኑ አሸንፈን መውጣት ችለናል፡፡ “
” ቡድኑ በመከላከል ረገድ በፊትም ጥሩ ነበር ። አሁን ላይ የፊት መስመሩን ለማጠናከር እየጣርን ነው። ዛሬ ጥሩ ነገር ተመልክቻለው። በቀጣይ 4 እና 5 ጨዋታዋች ወደ ጥሩ አቋም መምጣት እንችላለን፡፡ ደጋፊዎቻችንም በጣም አስደሳች ነበሩ። ከኛ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ። ዛሬ ይህንን ነው የተረዳሁት ፡፡ “
በአዳማ ከተማ በኩል አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ለቃለ መጠይቅ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡