ዋልያዎቹ እና አማቩቢዎቹ ወደ ሞሮኮ 2018 ለማምራት ካፍ ሁለተኛ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ነገ 10፡00 ላይም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አዲስ አበባ ስታድየም ያደርጋሉ።
ግብፅ ኬንያን ተክታ በ2018ቱ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ላይ እንድትሳተፍ የቀረበላትን ጥያቄ ወደ ጎን በማለቷ ካፍ ለኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ወደ ውድድሩ የመመለስ ሁለተኛ የማጣሪያ ዕድል መስጠቱ ሰሞነኛ ዜና ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ጨዋታው እንዲራዘምለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ካፍ ባስቀመጠው ፕሮግራም መሰረት ሁለቱ ቡድኖች ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል ።
በውዝግቦች የተሞላው የአሰልጣኝ አሸነፊ በቀለ ስብስብ ለቻን ለማለፍ በዞኑ ከሱዳን ጋር ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታ በሜዳው 1-1 ተለያይቶ ከሜዳው ውጪ በኤልሳምኒ ኤልሳዊ የ47ደቂቃ አስደናቂ ጎል 1-0 በመረታቱ በድምር ውጤት 2-1 ተሽንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኖ ነበር። በተመሳሳይ ወቅት በዞኑ ጠንካራ ከሆነው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተደልድላ የነበረችው ሩዋንዳ ከሜዳዋ ውጪ ባደረገችው የመጀመሪያ ጨዋታ 3-0 ተሸንፋ የነበረ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ 2-0 ማሸነፍ ብትችልም ድሉ ወደቻን ሊያሻግራት ሳይችል ቀርቷል። የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከቻን ማጣሪያ ስንብት በኃላ ሌላ ጨዋታ ያላደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ባገኘችው የወዳጅነት ጨዋታ ዕድል ሞሮኮን ገጥማ 4-0 ተሸንፋለች ።
ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ማድረግ እና አለመድረጉ ሳይለይለት በፊት ጥሪ ተደርጎላቸው የመጡ ተጫዋቾችን ከበተነ በኃላ በድጋሚ በመጥራት ከትናንት በስትያ ጀምሮ ዝግጅቱን አድርጓል። ኄኖክ አዱኛ ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና እሸቱ መናም በቡድኑ ውስጥ እንደአዲስ የተካተቱ ተጨዋቾች ሆነዋል። ዘግየት ብሎ ወደ አዲስ አበባ የገባው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ 8 ያህል በመጀመሪያው ማጣሪያ ላይ ያልተሳተፉ ተጨዋቾችን በማካተት ለነገው ጨዋታ እንደሚቀርብ ይጠበቃል ።
በቅርብ አመታት ከተመለከትናቸው ብሔራዊ ቡድኖቻችን በሁሉ ረገድ እጅግ ደካማ የሆነው የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ወቅቶች ከሜዳ ውጪ በሚነሱ ጉዳዮች ሲታመስ እና በሜዳ ላይም ደካማ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። የቡድኑ የወረደ የማሸነፍ ተነሳሽነት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሽቆለቁል ውጤትም አጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡ ተስፋ እንዲቆርጥ የደረገ ሆኗል፡፡ ሽንፈቶቹንም በቁጭት ሳይሆን በስላቅ መልክ እንዲያያቸው መንስኤ የሆነ ይመስላል። ሽንፈቱ ከሚያበሳጨው ሰው የበለጠ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ ግድ የማይሰጠው እና “ድሮም የኢትዮጵያ ኳስ” የሚል አስተያየት መብዛቱ ብሔራዊ ቡድኑ ያለበትም ወቅታዊ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
በወቅቱ የሀገሪቱ የእግር ኳስ ዋነኛ መነጋገሪያ ከሆነው ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የምርጫ ሂደት እና ከሊጉ ጅማሮ ጥላ ስር ሆኖ በጥቂት ቀናት ዝግጅት ለነገው ጨዋታ የሚቀርበው ቡድን አሁንም በብዙዎች ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ ነው። ቡድኑ የተገኘውን ሁለተኛ ዕድል ተጠቅሞ ለውድድሩ የሚያልፍ ከሆነ በውድድሩ ላይ በመሳተፍ ከሚያገኘው ጥብመም ይልቅ ያለበትን ጫና ከለመቀነስ፣ የህዝቡን ተኩረተ በመጠኑ ከማግኘት እና ከተደጋጋሚ ሽንፈት ከሚመጣ ተነሳሽነት ማጣት በጥቂቱ ከማገገም አንፃር ጥሩ ዕድል ሊፈጥርለት እንደሚችል ቢጠበቅም ሽንፈት ካስተናገደ ግን ከበፊቱም በባሰ መልኩ ጫና ውስጥ የሚከተው ከመሆኑም በላይ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ወንበር የሚያነቃንቅም ይሆናል፡፡
የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ አሰልጣኝነቱ ከመጡ በኋላ ቡድኑ ባደረጋቸው 8 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ጅቡቲን ብቻ ሲሆን ጎል ማስቆጠር የቻለውም በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው፡፡ ይህም ከሚሌንየሙ ወዲህ እጅግ ደካማው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያደርገዋል፡፡