የሴካፋ የክለቦች ዋንጫ ዛሬ በታንዛንያ ዳሬሰላም ይጀመራል፡፡ በውድድሩ አዳማ ከነማ ለ2ኛ ተከታታይ አመታት ኢትዮጵያን በመወከል በክለቦች ውድድሩ ላይ ይሳተፋል፡፡ እኛም ለግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ ውድድሩን የተመለከቱ እውነታዎችን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ካጋሜ ካፕ
-የኢትዮጵያ ክለብ ይህንን ውድድር አሸንፎ አያውቅም፡፡
-ኢትዮጵያ ይህንን ውድድር አስተናግዳ አታውቅም፡፡
-ከኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በውድድሩ የተካፈለው ክለብ ኤሌክትሪክ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 ከያንጋ አፍሪካ ጋር ያደረገው የመጀመርያ ጨዋታንም 0-0 በሆነ ውጤት አጠናቋል፡፡ ቡድኑ በዚህ ወድድር ከ3 ጨዋታ 2 ነጥብ ብቻ ሰብስቦ ከምድቡ ተሰናብቷል፡፡
-በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ክለቦች 5 ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 7 ጊዜ በመሳተፍ ቅድሚያውን ሲይዝ ኤሌትሪክ 3 ጊዜ አዳማ ከነማ እና ሀዋሳ ከነማ 2 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 1 ጊዜ ተሳትፈዋል፡፡
-ከኢትዮጵያ ክለቦች የመጀመርያውን ድል ያስመዘገበው ክለብ በ2001 የጅቡቲው ሲዲኤን 3-0 ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ አቻ የወጣው ደግሞ በ1994 ከያንጋ አፍሪካ 0-0 የተለያየው ኤሌክትሪክ ነው፡፡ በሽንፈትም የመጀመርያው ኤሌክትሪክ ነው፡፡ (በቪላ 4-1)
-ከኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛውን ውጤት ያመጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ በ2010 እስከ ፍፃሜው መድረስ ሲችሉ በፍፃሜው በኤ.ፒ.አር 2-0 ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል፡፡ ከጊዮርጊስ የፍፃሜ ፍልሚያ ቀጥሎ በትልቅነቱ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ ቡና በ1998 እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2001 እና 2007 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡
-ከኢትዮጵያ ክለቦች በአንድ ጨዋታ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ በ2011 የጅቡቲው ፖርት ኤኤስን 7-0 ያሸነፈበት ውጤት በከፍተኛነቱ ተመዝግቧል፡፡
-ከኢትዮጵያ ክለቦች አንድ ጨዋታ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረባቸው ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከነማ ናቸው፡፡ በ1999 በሩብ ፍፃሜው በዩጋንዳው ቪላ 4-1 አምና በተደረገው ውድድር ደግሞ አዳማ ከነማ በታንዛንያው አዛም 4-1 ተሸንፈዋል፡፡
——————————————————————————————–
የካጋሜ ካፕ አጠቃላይ እውነታዎች
-የሴካፋ ክለቦች ዋንጫ እ.ኤ.አ. በ1967 ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ሲሆን የኬንያው ክለብ አባሉህያ ኤፍሲ (ያሁኑ ኤኤፍሲ ሊዮፓርድስ) ውድድሩን ማሸነፍ የቻለ የመጀመሪያው ክለብ ነበር። አባሉህያ ዋንጫውን ማንሳት የቻለው የታንዛንያውን ሰንደርላንድ ክለብ በፍፃሜው ጨዋታ 5-0 በመርታት ነበር።
– የታንዛንያው ክለብ ሲምባ የሴካፋ ክለቦች ውድድርን 6 ጊዜ በማሸነፍ ባለሪከርድ ነው። ክለቡ ለፍፃሜ 11 ጊዜ ቀርቦ በ1974፣ 1991፣ 1992፣ 1995 እና በ2002 ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። ሲምባ በ5 የፍፃሜ ጨዋታዎች በመሸነፍም ከሩዋንዳው ኤፒአር ክለብ ጋር ቀዳሚ ነው።
– በሃገራት ደረጃ የኬንያ ክለቦች ውድድሩን ለ15 ጊዜ በማሸነፍ የሚስተካከላቸው የለም። የታንዛኒያ ክለቦች 11 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን ሁለተኛ ሲሆኑ ዩጋንዳ በ5፣ ሩዋንዳ በ4፣ ሱዳን በ3 እንዲሁም ብሩንዲ በ1 ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።
– ውድድሩ በሙሉ ስሙ የሴካፋ ካጋሜ ካፕ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የሩዋንዳው ፕሬዘዳንት በአመት 60ሺህ ዶላር በመክፈል ስፖንሰር ያደርጉታል። ይህ ገንዘብ ለውድድሩ አሸናፊዎች በሽልማት መልክ የሚሰጥ ሲሆን ለሻምፒዮኑ ክለብ 30ሺህ፣ ለ2ኛው 20ሺህ እንዲሁም ለ3ኛው 10ሺህ ዶላር ይደርሳቸዋል።
– በአሁኑ ወቅት የኬንያውን ክለብ ሶፋክፓ እያሰለጠነ የሚገኘው ዩጋንዳዊ ሳም ቲምቤ የሴካፋ ክለቦች ዋንጫን ለ5 ጊዜ በአሠልጣኝነት በማንሳት ሪከርዱን ይዟል። አሠልጣኙ በ2004 ከኤስሲ ቪላ፣ በ2005 ከፖሊስ ኤፍሲ፣ በ2009 ከአትራኮ እንዲሁም በ2011 ከያንግ አፍሪካንስ ክለቦች ጋር ውድድሩን ማሸነፍ ችሏል።
– በ8 የተለያዩ አጋጣሚዎች ሁለት የአንድ ሃገር ክለቦች ለፍፃሜ መድረስ የቻሉ ሲሆን ይህም በኬንያ እና ታንዛንያ ክለቦች ብቻ ይህንን ማሳካት ችለዋል። እነዚህም ሲምባ ከ ያንግ አፍሪካ በ1975፣ 1992፣ 2011 ጎር ማሂያ ከ ሊዮፓርድስ በ1980፣ 1985 ሊዮፓርድስ ከኬንያ ብሪወሪስ (ያሁኑ ተስከር ክለብ) በ1997 እንዲሁም ያንግ አፍሪካ ከ አዛም ክለብ በ2012 የተገናኙባቸው ጨዋታዎች ናቸው።
– ታንዛንያ ውድድሩን ለ11 ጊዜያት በማስተናገድ ቀዳሚ ስትሆን የዘንድሮው ውድድር 12ተኛዋ ይሆናል። ኬንያ በ9፣ ዩጋንዳ በ6 ይከተላሉ።