የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ በ2017 ቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ የግብፁ አል አህሊን በአጠቃላይ ውጤት 2-1 በመርታት በታሪኩ ለሁለተኛ ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ ከሳምንት በፊት አሌክሳንደሪያ ላይ የአቻ ውጤት ይዞ የተመለሰው ዋይዳድ በሜዳው አህሊን 1-0 በመርታት ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡
በስታደ መሐመድ አምስተኛ በተደረገው ጨዋታ አል አህሊ የመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ላይ በኳስ ቁጥጥር ብልጫን ተጋጣሚው ላይ በመውሰድ ተጭኖ ለመጫወት ሲሞክር ዋይዳዶች በመከላከሉ ደረጃ ጥብቅ ነበሩ፡፡ አብደላዲም ካርዱፍ የሞከረው ሙከራ የግብ አግዳሚ ሲመልስበት በ34ኛው ደቂቃ በመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው የአህሊው አማካይ ሞሜን ዛካሪያ ከዋይዳድ ግብ ጠባቂ ዞሂር ላሮቢ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ላሮቢ በግሩም ሁኔታ ኳስ ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ዋይዳድ መሻሻሎችን በማሳየት አህሊ ላይ ጫና ማሳደር ሲችል በጨዋታው ላይ የተሻለ መንቀሳቀስ ያልቻለው የአህሊው አጥቂ ዋሊድ አዛሮ በመቀየር የማጥቃት አማራጫቸው ለማስፋት አህሊዎች ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ በ69ኛው ደቂቃ አሽራፍ ቤንሻሪኪ ያሻገረውን ኳስ ዋሊድ ኤል ካርቲ አስቆጥሮ ዋይዳድን መሪ አድርጓል፡፡ አሃሊዎች በተለይ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ዋይዳድ በደጋፊዎች ፊት ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡
ዋይዳድ ሞሮኳዊው ፖለቲከኛ እና የሪል-ስቴት ቢዝነስ ባለቤት ሰዒድ ናሲሪን ፕሬዝደንት አደርጎ ከሾመ በኃላ በስኬት ጎዳና መጓዙን ቀጥሏል፡፡ ሰዒድ ወደ ዋይዳድ ሲመጡ ክለቡ ለአራት አመታት ዋንጫ አሸንፎ የማያውቅ ሲሆን ከሳቸው በኃላ ግን የሞሮኮ ቦቶላ ሊግን እና አሁን ደግሞ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ እንዲሁም ክለቡ ከነበረበት እዳ ነፃ እንዲሆን አስችለዋል፡፡
አሰልጣኝ ሁሴን አሞታ ፉስ ራባትን የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ካደረገ በኃላ አሁን ደግሞ ከዋይዳድ ጋር የአፍሪካን ትልቁን የክለቦች ውድድር ማሸነፍ ችሏል፡፡ ዋይዳድ የቻምፒየንስ ሊጉን ለማንሳት 25 ዓመታት መታገስም አስፈጎታል፡፡ ከዋይዳድ ውጪ ፋር ራባት በ1985፣ ራጃ ካዛብላንካ በ1989፣ 1997 እና 1999 ዋንጫውን ማሸነፍ የቻሉ ሌሎቹ የሞሮኮ ክለቦች ናቸው፡፡
ዋይዳድ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ የ2.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ሲያገኝ አፍሪካን ወክሎ በታህሳስ ወር በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ በዚህም ተሳትፎ ተጨማሪ እስከአንድ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት የሚያገኝ ይሆናል፡፡