​የእለቱ ዜናዎች፡ ማክሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2010 

ጠቅላላ ጉባዔ 

ጥቅምት 30 በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል እንዲደረግ ቀጠሮ የተያዘለት የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ የሚደረግበት ቀን እየቀረበ በመጣ ቁጥር እጅግ በርካታ የሴራ ንድፈ ኃሳቦች እየተሰሙ እና አስገራሚ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል። አቶ ጁነይዲ ባሻ የምርጫው ሂደት ፊፋ ሊያጤነው ይገባል ብለው ደብዳቤ መላካቸውን ተከትሎ ፊፋ  ጠቅላላ ጉባኤ መደረጉን ደግፎ ምርጫው እንዲዘገይ መልዕክት መላኩ ይታወቃል። ቀጥሎም የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ከነባር ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም ከአንድ እጩ ፕሬዝደንት ትዕዛዝ ተቀብለው “የነበሩ የአሰራር ክፍተቶች ታርመዋል፣ በጠቅላላ ጉባኤው ዕለት ምርጫውን ማድረግ የሚቻል ስርአት ተበጅቷል እና ፊፋ ምርጫው ይዘገይ የሚለውን ውሳኔ ይቀይር” የሚል ደብዳቤ እንደላኩ የታወቀ ሲሆን ፊፋም ዛሬ ለደብዳቤው አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ምርጫው በጠቅላላ ጉባኤው እለት እንዲካሄድ የሚፈቅድ ደብዳቤ መላኩ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ለፊፋ የተላከው ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት እውቅና ውጪ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነይዲም ለፊፋ ያለውን ሁኔታ የሚገልፅ ሌላ ደብዳቤ መላካቸው ታውቋል፡፡

ምርጫው በዚህ መንገድ ጥቅምት 30 ከተካሄደ አንዳንድ ክልሎች ጉባዔውን ረግጠው ሊወጡ እንደሚችሉም ተነግሯል፡፡ 

ጅማ አባ ቡና 

በሀዋሳ ከተማ እና በኢትዮ ኤሌትሪክ መካከል የተደረገው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በተደረገ የውጤት ማጭበርበር ቡድኔ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንድወርድ ተደርጓል በሚል ጅማ አባ ቡና ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ አቅርቦ ጉዳዩ ለረጅም ወራት ሲታይ ቆይቶ ቅሬታው ውድቅ መሆኑ ይታወሳል። አሁን ጅማ አባቡና ውሳኔውን ተከትሎ ቀጣይ የክለቡ አቋም ምን እንደሆነ ላነሳነው ጥያቄ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋለም ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡ ” ፍርደ ገምድል በሆነው ውሳኔው አዝነናል በቀጣይ በውሳኔው ዙርያ የክለቡ አቋም ምን እንደሆነ ከህግ ባለሙያዎች ጋር ተመካክረን አንድ ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል፡፡ አቶ ይርጋለም አክለውም ክለቡ በከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 

በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፋሲል ከተማ እና ሻሸመኔ ከነማ መካተታቸውን ተከትሎ ህዳር 2 እና 3 ይጀመራል ተብሎ መርሀ ግብር የወጣለት ቢሆንም አዲሶቹ ቡድኖች የዝግጅት ጊዜ እንዲያገኙ እና የውድድሩ አዲስ ፕሮግራም እስኪሰራ ጊዜ በማስፈልጉ መክፈቻ ጨዋታው ወደ ህዳር 9 እና 10 መራዘሙ ይታወቃል። ሆኖም የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ አስቀድሞ በወጣለት መርሀ ግብር ህዳር 2 እና 3 በአአ እና በክልል ከተሞች የሚካሄድ ይሆናል።

ጋምቤላ

የአፋር ፣ የሐረሪ ፣ የጋምቤላ እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ትላንት በኢትዮዽያ ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔውን አስመልክቶ በጋራ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል። ዛሬ ደግሞ ያለፉትን አመታት የጋምቤላ ክልልን በመወከል በስራ አስፈፃሚነት የሰሩት እና አሁን ለዳግመኛ አራት አመት በድጋሚ የጋምቤላን ክልል በመወከል በእጩነት የተመረጡት ኢንጂነር ቾል ቤል ትላንት የተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ የጋምቤላ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን የማያውቀውና መግለጫው ላይ የተገኙትም ግለሰብ የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም መንግስትን እንደማይወክሉ አስታውቀዋል፡፡

ዝውውር

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር አመት የተጨዋቾች ዝውውር በይፋ ተጠናቀቀ፡፡  በዘንድሮ አመት ከፍተኛ የዝውውር ገበያ ያደረጉት 16ቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በርካታ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ በማምጣት ጅማ አባ ጅፋር ቀዳሚ ሲሆን ጥቂት ተጨዋቾችን በማስፈረም መከላከያ ይጠቀሳል። ከአነስተኛው 40ሺህ ወርሀዊ ደሞዝ አንስቶ ከፍተኛ ወርሀዊ ደሞዝ እስከ ሆነው 170 ሺህ ብር ድረስ ክለቦች ለዝውውር ያወጡት የክፍያ መጠን ነው።

ብሔራዊ ቡድን 

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን እሁድ የመጀመርያውን የቻን የማጣርያ ጨዋታውን በሩዋንዳ 3-2 ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ ዛሬ 04:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምዱን የሰራ ሲሆን በ24 ሰአት ውስጥ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ መጫወት የቻለው የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በዛሬው ልምምድ እረፍት እንዲያደርግ ተብሎ ልምምድ ሳይሰራ ቀርቷል፡፡ የተቀሩት ተጨዋቾች በሙሉ ግን ልምምድ እንደሰሩ ተመልክተናል። በፓስፖርት ጉዳይ የመጀመርያው ጨዋታ ያመለጣቸው ተጫዋቾች አሁንም የፓስፖርት ጉዳያቸው የማለቁ ነገር አጠራጣሪ መሆኑ እየተሰማ ሲሆን ምናልባት የተባለው እውነት ከሆነ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሌሎች ተጨዋቾችን የመጥራት ግዴታ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እሁድ ሩዋንዳ ላይ የሚደረገውን የመልሱ ጨዋታን አራቱም ዳኞች ከሱማልያ ሲሆኑ የጨዋታው ኮሚሽነር ከቡሩንዲ ናቸው።

ኢትዮዽያ ቡና 

በ2008 የውድድር አመት ኢትዮዽያ ቡናን የተቀላቀለው ናይጄርያዊው ተከላካይ ኢኮ ፌቮ ክለቡ በዲሲፒሊን ጥሰት እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንደቀጣው የተሰማ ሲሆን ወደፊት ክለቡ ውሳኔውን ካልቀየረ በቀር ይህን አመት በኢትዮዽያ ቡና ማልያ ላንመለከተው እንደምንችል ከውሳኔው መረዳት ይቻላል። ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና ማሊያዊ አጥቂ ያስመጣ እንደሆነ ቢገለፅም የዝውውር መስኮቱ መዘጋቱን ተከትሎ የተጨዋቹ የዝውውር ሁኔታ ላይጠናቀቅ እንደቻለም ሰምተናል።

ከፍተኛ ሊግ 

ህዳር 9 እና 10 የሚጀምረው የከፍተኛ ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ተሳታፊ ቡድኖች የምዝገባ እና የዳኞች የታዛቢዎች ለፌዴሬሽኑ መከፈል ያለበት የገንዘብ መጠን የተወሰኑ ክለቦች የከፈሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ክለቦች ክፍያውን ያላጠናቀቁ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። ክፍያውንም ያላጠናቀቁ ክለቦች በፍጥነት ክፍያቸውን እንዲያጠናቅቁ ፌዴሬሽኑ አሳስቧል።

ከ17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን 

የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ ጋር ላለበት የማጣርያ ጨዋታ ቅድመ ዝግጅቱን ለማድረግ ለፌዴሬሽኑ አሰልጣኞቹ እቅዳቸውን ያስገቡ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ በማጣት ምክንያት ልምምዳቸውን ያልጀመሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሶከር ኢትዮዽያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አብዛኛዎቹ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በጠቅላላ ጉባዔው ጉዳይ ላይ ተጠምደው ስለ ታዳጊ ቡድኑ ትኩረት አለመስጠታቸው እንደሆነ ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *