የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ዛሬ ተጀምሯል

የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ዛሬ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተጀምሯል፡፡ የአምናው ቻምፒዮን ደደቢት እና ድሬዳዋ ከተማ የሜዳቸውን ጨዋታዎች ሲያሸንፉ ንግድባንክ እና መከላከያ ከሜዳቸው ውጪ ድል አድርገዋል፡፡


ደደቢት 3-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

(ዳዊት ጸሀዬ)

አዲስአበባ ላይ የተደረገው የደደቢትና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ እንደከዚህ ቀደም አመታት ሁሉ በስታዲየሙ የፀጥታ አካላት አስቀድመው ባለመገኘታቸው የስፓርት ቤተሰቡ ላልተፈለገ መጉላላት ሲዳረግ ተመልክተናል፡፡ ይባስ ብሎ የውድድር አመቱ የመክፈቻ ጨዋታ እንደመሆኑ ጨዋታውን ለማስጀመር ምንም አይነት የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የተወከለ ሰው በጨዋታው አለመገኘቱ ሌላው አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡

በዚህ መልኩ በተጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተጋጣሚያቸው ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስን መስርተው እንዳይወጡ በማድረግ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል ፤ ነገርግን ደደቢቶች ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በተለይም በ20ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት አክርራ መትታ የግቡ ቋሚ የመለሰባት እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ እፀገነት ብዙነህ ያቀበለቻትን ኳስ ተጠቅማ ሎዛ አበራ ከኤሌክትሪክ የግብ ክልል ጠርዝ የሞከረቸውና የግቡ ቋሚ የመለሰባት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡
በ21ኛው ደቂቃ ልማደኛዋ ግብ አዳኝ ሎዛ አበራ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርራ በመምታት ቡድኗን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ አስቆጥራለች፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በይበልጥ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ደደቢቶች ክለቡን በክረምቱ የዝውውር መስኮት የተቀላቀለችውና በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰችው እፀገነት ብዙነህ ያቀበለቻትን ኳስ ተጠቅማ ሰናይት ባሩዳ የቡድኗን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

ከእረፍት መልስም በደደቢቶች የበላይነት በታየበት በዚሁ ጨዋታ የጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ ኤሌክትሪክ የሜዳ ክፍል አጋድሎ ተከናውኗል፡፡ በ57ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ በግሩም አጨራረስ ለራሷ ሁለተኛ እንዲሁም ለቡድኗ ሶስተኛና የማሳረጊያውን ግብ አስቆጥራ የቡድኗ የውድድር ዘመኑን በጥሩ አጀማመር እንዲጀምር አስችላለች፡፡

ሲዳማ ቡና 2-6 መከላከያ

(ቴዎድሮስ ታከለ)

በክረምቱ ጥቂት ነገር ግን ወሳኝ ግዢዎችን የፈፀመው መከላከያ ከሜዳው ዊጪ የአምናው ክስተት ሲዳማ ቡና ላይ የግብ ናዳ አውርዷል፡፡ ጨዋታው ግማሽ ሰአት እሲቆጠር ድረስ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በ31ኛው ደቂቃ ላይ ምህረት መለሰ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ የሲዳማ ቡናን የተከላካይ መስመር ስትረብሽ የነበረችው አዲሷ ፈራሚ መዲና አወል ክለቧን ቀዳሚ ካደረገች በኋላ የጎል መንገዱ ወለል ብሎ ተከፍቷል፡፡
በ42ኛው ደቂቃ ላይ በመሀል ሜዳው አጋማሽ ላይ የሲዳማ ቡናዋ አምበል ነፃነት ፀጋዬና የመከላከያዋ አጥቂ ብሩክታዊት አየለ በድንገት ተጋጭተው የስፖርት ቤተሰቡን ያስደነገጠ ጉዳት በሁለቱም ላይ በመድረሱ በአፋጣኝ ወደ ህክምና በአምቡላስ ተወስደዋል፡፡ ነፃነት ጭንቅላቷ ብሩክታዊት ደግም ፊቷ ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ጨዋታው ጉዳት በመከሰቱ ምክንያት 10 ያህል ደቂቃ ከተቋረጠ በኃላ ሲቀጥል የብሩክታዊትን መጎዳት ተከትሎ ተቀይራ የገባችው ሄለን እሸቱ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጣ የመከላከያን መሪነት ወደ ሁለት አስፍታለች፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ደግሞ የምስራች ላቀው ከግራ መስመር ሰብራ በመግባት ሶስተኛውን ግብ አስቆጥራ በመከላከያ 3-0 መሪነት የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያወች የበላይነት ይበልጥ የሰፋበት ነበር፡፡ በ46ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ በግል ጥረቷ ተጫዋቾችን በማለፍ ያቀበለቻትን ኳስ በእለቱ ምርጥ እንቅስቃሴን ስታደርግ የነበረችው መዲና አወል ለራሷ 2ኛ ለክለቧ 4ኛውን ግብ አስቆጥራለች፡፡ በግሏ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ቱሪስት ለማ በ57ኛው ደቂቃ አስቆጥራ ሲዳማዎችን ብታነቃቃም ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ሄለን እሸቱ ለራሷ እና ሁለተኛ ለመከላከያ 5ኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

73ኛው ደቂቃ ላይ ምህረት መለስ ለመከላከያ 6ኛውን ግብ ስታስቆጥር ጨዋታው ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው ሲዳማ ቡናዎች በመሀሪ በቀለ አማካኝነት 2ኛ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው በመከላከያ 6-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

አዳማ ከተማ 2-3 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አምና ሊጉን በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃነት ያጠናቀቁት ሁለቱ ቡድኖች ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር አድርገው በመጨረሻም የ3 ጊዜ የሊግ  ቻምፒዮኑ ንግድ ባንክ አሸናፊ ሆናል፡፡

በጨዋታው 9ኛው ደቂቃ ላይ በአምበሏ ረሂማ ዘርጋ አማካኝነት ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ንግድ ባንኮች ነበሩ፡፡ አዳማዎች በ22ኛው እና 29ኛው ደቂቃ ዮዲት መኮንን እና ይታገሱ ገ/ፃድቅ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ወደ መሪነት ሲሸጋገሩ ህይወት ደንጊሶ በ43ኛው ደቂቃ ባንክን አቻ አድርጋለች፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ጎል ለማስተናገድ ረጅም ደቂቃዎች የፈጀ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ የመስመር ተከላካይዋ ሐብታም እሸቱ ያስቆጠረችው ጎል የማታ ማታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ድል አስጨብጣለች፡፡


ድሬዳዋ ከተማ 2-1 ሀዋሳ ከተማ

(ዳንኤል መስፍን)

በክረምቱ ልምድ ያካበቱ እና ተስፈኛ ተጫዋቾችን የሰበሰበው ድሬዳዋ ከተማ በተቃራኒው ወሳኝ ተጫዋቾቹን ያጣው ሀዋሳ ከተማን 2-1 አሸንፎ አጀማመሩን አሳምሯል፡፡

በዛሬው ጨዋታ በፍጥነት ወደ ጎል የሚደረግ እንቅስቃሴ እና ጥሩ የኳስ ፍሰት የተመለከትን ሲሆን ድሬደዋ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በ29ኛው ደቂቃ ያብስራ ይታደል ድሬዳዋን ቀዳሚ ስታደርግ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀዋሳ ከተማ ምርቃት ፈለቀ ባስቆጠረችው ጎል አቻ ሆኗል፡፡ ሆኖም የአቻነት ጎሉ የዘለቀው ለሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ስራ ይርዳው ድሬዳዋ ከተማን ለአሸናፊነት ያበቃች ጎል አስቆጥራለች፡፡

የአንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ነገ ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ጌዲኦ ዲላ 09:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *